ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ ወደሚገኙት፣ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ከተሞች በቀረበ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደዚያም ስትገቡ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወደዚህ አምጡት። ማንም፣ ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል’ በሉት።” የተላኩትም ሄደው ልክ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት። ባለቤቶቹም ውርንጫውን ሲፈቱ አይተው፣ “ውርንጫውን ለምን ትፈታላችሁ?” አሏቸው። እነርሱም፣ “ለጌታ ያስፈልገዋል” አሉ። ከዚያም ውርንጫውን ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልብሶቻቸውን በላዩ ጣል አድርገው ኢየሱስን በውርንጫው ላይ አስቀመጡት። ሰዎችም እርሱ በሚሄድበት መንገድ ላይ ልብሶቻቸውን ያነጥፉ ነበር። በደብረ ዘይት ተራራ ቍልቍል ወደሚወስደው መንገድ በተቃረቡ ጊዜ፣ ቍጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ደቀ መዛሙርት ስላዩት ታምራት ሁሉ ደስ እያላቸው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ጀመር፤ “በጌታ ስም የሚመጣው ንጉሥ የተባረከ ነው!” “በሰማይ ሰላም፣ በአርያምም ክብር ይሁን!” በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት። እርሱም፣ “እላችኋለሁ፤ እነርሱ ዝም ቢሉ፣ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው። ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ፤ “ሰላምሽ የሚሆነውን ምነው አንቺ ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ! አሁን ግን ከዐይንሽ ተሰውሯል፤ ጠላቶችሽ ዙሪያሽን ቅጥር ሠርተው፣ ከየአቅጣጫውም ከብበው አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣልና፤ አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ የመጐብኛሽን ጊዜ አላወቅሽምና።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ ሻጮችን ከዚያ ያስወጣ ጀመር፤ ደግሞም “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው። በየቀኑም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ መሪዎችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ ሁሉ ከርሱ ጋራ ተቈራኝተው ትምህርቱን ይከታተሉ ስለ ነበር፣ የሚያደርጉት ግራ ገባቸው።
ሉቃስ 19 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 19
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 19:29-48
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች