ከአይሁድ አለቆች አንዱ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም፤ ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።” ሰውየውም፣ “እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እንግዲያውስ አንድ ነገር ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው በጣም ዐዘነ። ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነው! ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።” ይህን የሰሙ ሰዎችም፣ “ታዲያ፣ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስም፣ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ። ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የተወ፣ በዚህ ዘመን ብዙ ዕጥፍ፣ በሚመጣውም ዘመን የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ ነቢያት ስለ ሰው ልጅ የጻፉትም ሁሉ ይፈጸማል። ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያፌዙበታል፤ ያንገላቱታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል። እርሱ ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ይነሣል።” ደቀ መዛሙርቱ ግን ከዚህ ሁሉ የተረዱት አንድም ነገር አልነበረም፤ አባባሉም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለ ምን እንደ ተናገረም አላወቁም። ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ በቀረበ ጊዜ፣ አንድ ዐይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። ዐይነ ስውሩም ሕዝቡ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው” ብለው ነገሩት። እርሱም፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ጮኸ። ከፊት የሚሄዱ ሰዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ። ኢየሱስም ቆም ብሎ ሰውየውን ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ፤ ወደ እርሱም በቀረበ ጊዜ፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። ዐይነ ስውሩም፣ “ጌታ ሆይ፤ ዳግም እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “እይ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ማየት ቻለ፤ እግዚአብሔርንም እያከበረ ኢየሱስን ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
ሉቃስ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 18
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 18:18-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች