አንድ ቀን ኢየሱስ ድዳ ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣለት በኋላ ድዳው ሰው ተናገረ፤ ሕዝቡም ተገረመ። አንዳንዶቹ ግን፣ “በአጋንንት አለቃ፣ በብዔልዜቡል፣ አጋንንትን ያወጣል” አሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሊፈታተኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳይ ከርሱ ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ የሚለያይ ቤትም ይወድቃል። ሰይጣንም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ፣ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ ትናገራላችሁና። እንግዲህ እኔ አጋንንትን የማወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በማን ያወጧቸው ይሆን? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። እኔ ግን አጋንንትን የማወጣው በእግዚአብሔር ጣት ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ መጣች ዕወቁ። “ብርቱ ሰው በሚገባ ታጥቆ ቤቱን ከጠበቀ፣ ንብረቱ በሰላም ይቀመጣል። ነገር ግን ይበልጥ ብርቱ የሆነ ሰው መጥቶ ካጠቃውና ካሸነፈው ታምኖበት የነበረውን ትጥቁን ያስፈታዋል፤ ምርኮውንም ወስዶ ለሌሎች ያካፍላል። “ከእኔ ጋራ ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋራ የማይሰበስብ ይበትናል። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ፣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሳያገኝም ሲቀር፣ ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም በኋላ ሄዶ ሌሎች ከርሱ የከፉ ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆንበታል።” ኢየሱስ ይህን እየተናገረ እያለ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ “የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው” አለችው። እርሱ ግን፣ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ። ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ በሄደ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ታምራዊ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። የደቡቧ ንግሥት በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋራ ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ እርሷ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። የነነዌ ሰዎችም በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋራ ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፣ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ። “መብራት አብርቶ በስውር ቦታ ወይም ከእንቅብ በታች የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁን የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። የሰውነትህ መብራት ዐይንህ ናት፤ ዐይንህ ጤናማ ስትሆን መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፤ ዐይንህ ታማሚ ከሆነች ግን መላ ሰውነትህ የጨለመ ይሆናል። ስለዚህ በውስጥህ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ከሆነና የጨለመ የሰውነት ክፍል ከሌለበት፣ የሰውነትህ ሁለንተና መብራት በወገግታው ያበራልህ ያህል ይደምቃል።” ኢየሱስ ንግግሩን እንደ ጨረሰ፣ አንድ ፈሪሳዊ ከርሱ ጋራ ምግብ እንዲበላ ጋበዘው፤ እርሱም ዐብሮት ገብቶ በማእድ ተቀመጠ። ፈሪሳዊውም ኢየሱስ ከምግብ በፊት እጁን እንዳልታጠበ ባየ ጊዜ ተደነቀ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጫዊ ክፍል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት የተሞላ ነው። እናንተ ሞኞች፤ የውጭውን የፈጠረ የውስጡንም አልፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል። “እናንተ ፈሪሳውያን ግን ወዮላችሁ፤ ከአዝሙድና ከጤና አዳም እንዲሁም ከአትክልት ሁሉ ዐሥራት ታወጣላችሁ፤ ሆኖም ፍትሕንና እግዚአብሔርን መውደድ ቸል ትላላችሁ፤ ነገር ግን ያን ሳትተዉ ይህኛውን ማድረግ በተገባችሁ ነበር። “እናንተ ፈሪሳውያን ወዮላችሁ፤ በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫ፣ በገበያ ስፍራ የአክብሮት ሰላምታ ትወድዳላችሁና። “ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበትን የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፣ ወዮላችሁ።” ከሕግ ዐዋቂዎች አንዱ መልሶ “መምህር ሆይ፤ እንዲህ ስትናገር እኮ እኛንም መስደብህ ነው” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ ሕግ ዐዋቂዎችም ደግሞ ወዮላችሁ፤ ሰዎች ሊሸከሙ የማይችሉትን ከባድ ሸክም ታሸክማላችሁ፤ እናንተ ራሳችሁ ግን በጣታችሁ እንኳ አትነኩትም። “አባቶቻችሁ የገደሏቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምታበጃጁ፣ ወዮላችሁ፤ እንግዲህ የአባቶቻችሁን ሥራ የምታጸኑ ምስክሮች ናችሁ፤ እነርሱ ነቢያትን ገደሉ፤ እናንተም መቃብራቸውን ታበጃጃላችሁ። ስለዚህም የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች፤ ‘ነቢያትንና ሐዋርያትን እልክላቸዋለሁ፤ እነርሱ አንዳንዶቹን ይገድላሉ፤ ሌሎችንም ያሳድዳሉ።’ ስለዚህ ይህ ትውልድ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ስለ ፈሰሰው፣ ስለ ነቢያት ሁሉ ደም ተጠያቂ ነው፤ ከአቤል ደም ጀምሮ፣ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ መካከል እስከ ፈሰሰው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ይፈለግበታል። አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ለዚህ ተጠያቂ ነው። “እናንተ ሕግ ዐዋቂዎች ወዮላችሁ! የዕውቀትን መክፈቻ ነጥቃችሁ ወስዳችኋልና፤ እናንተ ራሳችሁ አልገባችሁበትም፤ የሚገቡትንም ከልክላችኋል።” ኢየሱስ ከዚያ ከወጣ በኋላ፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ክፉኛ ይቃወሙትና በጥያቄም ያዋክቡት ጀመር፤ ከአፉ በሚወጣውም ቃል ሊያጠምዱት ያደቡ ነበር።
ሉቃስ 11 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 11:14-54
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች