ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎች ሰባ ሁለት ሰዎችን መርጦ ሾመ፤ ወደሚሄድበትም ከተማና ቦታ ሁሉ እንዲቀድሙት፣ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ ሠራተኞችን ወደ መከሩ እንዲልክ ለምኑት። ሂዱ፤ እንግዲህ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ኰረጆ ወይም ከረጢት ወይም ጫማ አትያዙ፤ በመንገድ ላይም ለማንም ሰላምታ አትስጡ። “ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ አስቀድማችሁ፣ ‘ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን’ በሉ፤ የሰላም ሰው በዚያ ካለ፣ ሰላማችሁ ያርፍበታል፤ አለዚያም ሰላማችሁ ለእናንተው ይመለሳል። ያቀረቡላችሁን ሁሉ እየበላችሁና እየጠጣችሁ በዚያ ቤት ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል። ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት አትዘዋወሩ። “ወደ ማንኛውም ከተማ ስትገቡ ሰዎቹ ከተቀበሏችሁ፣ ያቀረቡላችሁን ብሉ። በዚያ የሚገኙትን በሽተኞች እየፈወሳችሁ፣ ‘የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሏቸው። ነገር ግን ወደ አንድ ከተማ ገብታችሁ ካልተቀበሏችሁ፣ ወደ አደባባዩ ውጡና እንዲህ በሉ፤ ‘ለማስጠንቀቂያ እንዲሆናችሁ በእግራችን ላይ ያለውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች ይህን ዕወቁ።’ እላችኋለሁ፤ በዚያ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል። “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፤ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ልትዪ ነውን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።” ሰባ ሁለቱም ደስ እያላቸው ተመልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እንግዲህ እባቡንና ጊንጡን እንድትረግጡ፣ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጐዳችሁም አንዳች ነገር አይኖርም። ይሁን እንጂ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” በዚያ ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና። “ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ደግሞም ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብ ማን እንደ ሆነም ከወልድ በቀር፣ ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ የለም።” ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው፤ እላችኋለሁና፤ ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ፈልገው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ለመስማት ፈልገው አልሰሙም።”
ሉቃስ 10 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 10
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 10:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች