ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!” ማርያምም እንዲህ አለች፤ “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤ እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቷል፤ በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኗቸዋል፤ ገዦችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዷቸውን ሰድዷቸዋል፤ ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን እስራኤልን ረድቷል፤ ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”
ሉቃስ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 1:39-55
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos