የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 1:1-25

ሉቃስ 1:1-25 NASV

በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል፤ ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላለፉልን ነው። ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፤ እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፤ ይህንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች። ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ። አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ። ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር። የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል። ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን ዐውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤ እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር። ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በስተቀር መናገር ባለ መቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ። ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤ እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች።