ዘሌዋውያን 26:3-18

ዘሌዋውያን 26:3-18 NASV

“ ‘በሥርዐቴ ብትሄዱ፣ ትእዛዜንም በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣ ዝናብን በወቅቱ እሰጣችኋለሁ፤ ምድሪቱ እህሏን፣ የሜዳ ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። የምትወቁት እህል፣ የወይን ዘለላ እስከምትቈርጡበት ጊዜ፣ የምትቈርጡትም የወይን ዘለላ፣ እህል እስከምትዘሩበት ጊዜ ያደርሷችኋል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። “ ‘በምድሪቱ ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ ማንም አያስፈራችሁም። ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነርሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። ከእናንተ ዐምስቱ መቶውን፣ መቶውም ዐሥሩን ሺሕ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። “ ‘ፊቴን ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ እንድታፈሩና እንድትበዙም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋራ አጸናለሁ። የዓምናውን እህል እየበላችሁ ከጐተራው ሳያልቅ ለዘንድሮው እህል ደግሞ ቦታ ታስለቅቃላችሁ። ማደሪያዬን በመካከላችሁ አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁ እመላለሳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ። ለግብጻውያን ባሪያዎች እንዳትሆኑ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነት ቀንበራችሁን ሰብሬ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ። “ ‘ነገር ግን ባትሰሙኝ፣ እነዚህን ትእዛዞች ባትጠብቁ፣ ሥርዐቴን ብትንቁ፣ ሕጌን ብታቃልሉ፣ ትእዛዞቼንም ሁሉ ባለመፈጸም ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፣ እኔም ይህን አደርግባችኋለሁ፤ ድንገተኛ ድንጋጤ፣ የሚቀሥፍ በሽታ፣ ዐይናችሁን የሚያጠፋና ሰውነታችሁን የሚያመነምን ትኵሳት አመጣባችኋለሁ፤ እህል የምትዘሩት በከንቱ ነው፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ። “ ‘ከዚህ ሁሉ በኋላ ባትታዘዙኝ፣ ስለ ኀጢአታችሁ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ፤