ዘሌዋውያን 26:27-46

ዘሌዋውያን 26:27-46 NASV

“ ‘በዚህ ሁሉ ግን ባትታዘዙኝ፣ በእኔም ላይ ማመፃችሁን ብትቀጥሉ፣ እኔም በቍጣዬ እመጣባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም እኔው ራሴ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ። የወንዶች ልጆቻችሁን ሥጋና የሴቶች ልጆቻችሁን ሥጋ ትበላላችሁ። የኰረብታ መስገጃዎቻችሁን እደመስሳለሁ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁን አፈርሳለሁ፤ በድኖቻችሁን በድን በሆኑት ጣዖቶቻችሁ ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። ከተሞቻችሁን አፈራርሳለሁ፤ መቅደሶቻችሁንም ወና አደርጋለሁ፤ ጣፋጭ ሽታ ያለውን መሥዋዕታችሁንም አልቀበልም። በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻችሁ እስኪደነቁ ድረስ፣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ። በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ሰይፌን መዝዤም አሳድዳችኋለሁ። ምድራችሁ ባድማ፣ ከተሞቻችሁም ፍርስራሽ ይሆናሉ። ምድሪቱ ባድማ በሆነችበት ጊዜ ሁሉና እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር በምትኖሩበት ወቅት ምድሪቱ በሰንበት ዓመቷ ትደሰታለች፤ ምድሪቱም በሰንበቷ ታርፋለች፤ ትደሰታለችም። ምድሪቱ እናንተ በነበራችሁባት ጊዜ በሰንበት ያላገኘችውን ዕረፍት፣ ባድማ በምትሆንበት ጊዜ ሁሉ ታገኛለች። “ ‘ከእናንተ በሕይወት የተረፉትን፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ድንጋጤ እሰድድባቸዋለሁ፤ ነፋስ የሚያንቀሳቅሰው የቅጠል ድምፅ ያስበረግጋቸዋል፤ የሚያሳድዳቸውም ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሮጣሉ፤ ይወድቃሉም። የሚያሳድዳቸው ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት መቆም አትችሉም። በአሕዛብ መካከል ታልቃላችሁ፤ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። ከእናንተ የተረፉት በጠላቶቻቸው ምድር በራሳቸው ኀጢአትና በአባቶቻቸው ኀጢአት ምክንያት መንምነው ያልቃሉ። “ ‘ነገር ግን ለእኔ ያልታመኑበትንና በእኔም ላይ ያመፁበትን የራሳቸውን ኀጢአትና የአባቶቻቸውን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ይኸውም፣ እኔ ጠላት እንድሆንባቸውና ወደ ጠላቶቻቸው ምድር እንድሰድዳቸው ያደረገኝን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድና ስለ ኀጢአታቸው የሚገባውን ቅጣት ቢቀበሉ፣ በዚያ ጊዜ ከያዕቆብ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ከይሥሐቅም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ደግሞም ከአብርሃም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ ምድሪቱንም ዐስባታለሁ። ምድሪቱ እነርሱ ለቅቀዋት ስለ ሄዱ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱ በሌሉበት ጊዜም ባድማ ሆና በሰንበቷ ትደሰታለች፤ ሕጌን በማቃለላቸውና ሥርዐቴን በመናቃቸው፣ የኀጢአታቸውን ቅጣት ይቀበላሉ። በዚህ ሁሉ ግን ከእነርሱ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን በማፍረስ፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ፈጽሜ እስካጠፋቸው ድረስ አልተዋቸውም፤ አልጸየፋቸውምም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ። ስለ እነርሱም ስል፣ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው ጋራ የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” እግዚአብሔር በራሱና በእስራኤላውያን መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ በኩል ያቆማቸው ሥርዐቶች፣ ሕጎችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።