ዘሌዋውያን 1:1-14

ዘሌዋውያን 1:1-14 NASV

እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው፤ ከመገናኛውም ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ከእንስሳ ወገን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ። “ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከላሞች መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ ነቀፋ የሌለበትን ተባዕቱን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያቅርበው። የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል። ወይፈኑን በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን አምጥተው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት። እርሱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም ያውጣው። የካህኑ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ ዕንጨት ረብርበው እሳት ያንድዱበት። ካህናቱ የአሮን ልጆች ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምረው ብልቶቹን በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድሩት፤ አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መባውን ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። “ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን ያቅርብ። የሚቀርበውን መሥዋዕት ከመሠዊያው በስተሰሜን በኩል በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ሁሉ ይርጩት። አቅራቢው ብልቶቹን ያውጣ፤ ካህኑም ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምሮ በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድረው፤ አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑ መባውን ሁሉ አምጥቶ በመሠዊያው ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። “ ‘ለእግዚአብሔር በሚቃጠል መሥዋዕትነት የሚቀርበው መባ ከወፎች ወገን ከሆነ፣ ዋኖስ ወይም የርግብ ጫጩት ያቅርብ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}