ሰቈቃወ 5:1-22

ሰቈቃወ 5:1-22 NASV

እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኛ ላይ የደረሰውን ዐስብ፤ ውርደታችንን እይ፤ ተመልከትም። ርስታችን ለመጻተኞች፣ ቤቶቻችን ለባዕዳን ዐልፈው ተሰጡ። ወላጅ አልባና አባት የሌላቸው ሆንን፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆኑ። ለምንጠጣው ውሃ መክፈል ነበረብን፤ ዕንጨታችንንም የምናገኘው በግዢ ነበር። የሚያሳድዱን ከተረከዞቻችን ሥር ናቸው፤ ተጨንቀናል ዕረፍትም ዐጥተናል። እንጀራ እንጠግብ ዘንድ፣ ለአሦርና ለግብጽ እጃችንን ሰጠን። አባቶቻችን ኀጢአት ሠርተው ዐለፉ፤ እኛም የእነርሱን ቅጣት ተሸከምን። ባሮች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው ነጻ የሚያወጣን ማንም የለም። በምድረ በዳ ካለው ሰይፍ የተነሣ፣ በሕይወታችን ተወራርደን እንጀራ አገኘን። ቈዳችን እንደ ምድጃ ጠቍሯል፤ በራብም ተቃጥሏል። ሴቶች በጽዮን፣ ደናግል በይሁዳ ከተሞች ተደፈሩ። መሳፍንት በእነርሱ እጅ ተሰቀሉ፤ ሽማግሌዎችም አልተከበሩም። ጕልማሶች ወፍጮ እንዲፈጩ ተገደዱ፤ ወንዶች ልጆች በዕንጨት ሸክም ተንገዳገዱ። ሽማግሌዎች ከከተማዪቱ በር ሄደዋል፤ ጕልማሶች ዝማሬያቸውን አቁመዋል። ደስታ ከልባችን ጠፍቷል፤ ጭፈራችን ወደ ልቅሶ ተለውጧል። አክሊላችን ከራሳችን ላይ ወድቋል፤ ወዮልን፤ ኀጢአት ሠርተናልና! ከዚህ የተነሣ ልባችን ደከመ፤ ከእነዚህ የተነሣም ዐይናችን ፈዘዘ፤ ባዶዋን የቀረችው የጽዮን ተራራ፣ የቀበሮዎች መፈንጫ ሆናለችና። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ለዘላለም ትገዛለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። ስለ ምን ፈጽመህ ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረዥም ጊዜ ትተወናለህ? እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ፤ ፈጽመህ ካልጣልኸን፣ ከመጠን በላይ ካልተቈጣኸን።