ሰቈቃወ 3:1-36

ሰቈቃወ 3:1-36 NASV

በቍጣው በትር፣ መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ። ከፊቱ አስወጣኝ፤ በብርሃን ሳይሆን በጨለማ እንድሄድ አደረገኝ። በርግጥ ቀኑን ሁሉ በመደጋገም፣ እጁን በላዬ ላይ መለሰ። እርሱ ሥጋዬንና ቈዳዬን አስረጀ፤ ዐጥንቶቼንም ሰባበረ። በምሬትና በድካም፣ ቅጥር ሠራብኝ፤ ዙሪያዬንም ከበበኝ። ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደ ሆናቸው፣ በጨለማ እንድኖር አደረገኝ። በቅጥር ውስጥ ዘጋብኝ፤ ስለዚህ ማምለጥ አልቻልሁም፤ የእስር ሰንሰለቴንም አከበደብኝ። ርዳታ ፈልጌ ብጣራና ብጮኽ እንኳ፣ ጸሎቴን መስማት አልፈለገም። መንገዴን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤ ጐዳናዬንም አጣመመ። አሸምቆ እንደ ተኛ ድብ፣ እንደ አደባም አንበሳ፣ ከመንገድ ጐትቶ አስወጣኝ፤ ቈራረጠኝም፤ ያለ ረዳትም ተወኝ። ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻዎቹም ዒላማ አደረገኝ። ፍላጻዎችን ከሰገባው አውጥቶ፣ ልቤን ወጋው። ለሕዝቤ ሁሉ ማላገጫ ሆንሁኝ፤ ቀኑን ሙሉ በመሣለቅ ያዜሙብኛል። መራራ ሥር አበላኝ፤ ሐሞትም አጠገበኝ። ጥርሴን በድንጋይ ሰበረ፤ በትቢያ ውስጥ ረጋገጠኝ። ነፍሴ ሰላምን ዐጣች፤ ደስታ ምን እንደ ሆነ ረሳሁ። ስለዚህ፣ “ክብሬ፣ ከእግዚአብሔርም ተስፋ ያደረግሁት ሁሉ ሄዷል” አልሁ። የጭንቀቴንና የመንከራተቴን፣ ምሬትንና ሐሞትን ዐስባለሁ። ዘወትር አስበዋለሁ፤ ነፍሴም በውስጤ ተዋርዳለች። ሆኖም ይህን ዐስባለሁ፤ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው። ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።” እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው። ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን፣ ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው። ሰው በወጣትነቱ፣ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው። ብቻውን ዝም ብሎ ይቀመጥ፤ እግዚአብሔር አሸክሞታልና። ፊቱን በዐቧራ ውስጥ ይቅበር፤ ተስፋ ሊኖር ይችላልና። ጕንጩን ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ውርደትንም ይጥገብ። ጌታ ሰውን፣ ለዘላለም አይጥልምና፤ መከራን ቢያመጣ እንኳ ይራራል፤ ታላቅ ፍቅሩ አይለወጥምና። ሆነ ብሎ ችግርን፣ ወይም መከራን በሰው ልጆች ላይ አያመጣምና። የምድሪቱ እስረኞች ሁሉ፣ በእግር ሲረገጡ፣ በልዑል ፊት፣ ሰው መብቱ ሲነፈገው፣ ሰው ፍትሕ ሲጓደልበት፣ ጌታ እንዲህ ዐይነቱን ነገር አያይምን?