ሰቈቃወ 2
2
א አሌፍ
# 2 ይህ ምዕራፍ ጥቅሶቹ ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀምር፣ የመጀመሪያው ወይም የመጨረሻው መሥመር ትርጕም የሚሰጥ ቃል ወይም ዐረፍተ ነገር ያለው ግጥም ነው። 1ጌታ የጽዮንን ሴት ልጅ፣
በቍጣው ደመና እንዴት ጋረዳት!#2፥1 ወይም እግዚአብሔር በቍጣው የጽዮንን ሴት ልጅ እንዴት አዋረዳት!
ከሰማይ ወደ ምድር፣
የእስራኤልን ክብር ወርውሮ ጣለው፤
በቍጣው ቀን፣
የእግሩን መቀመጫ አላስታወሰም።
ב ቤት
2የያዕቆብን መኖሪያ ሁሉ፣
ጌታ ያለ ርኅራኄ ዋጣቸው፤
የይሁዳን ሴት ልጅ ምሽጎች፣
በቍጣው አፈረሳቸው፤
መንግሥቷንና መሳፍንቷን፣
በማዋረድ ወደ ምድር ጣላቸው።
ג ጊሜል
3በጽኑ ቍጣው፣
የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ#2፥3 ወይም ብርታትን ሁሉ፤ ወይም ንጉሥ ሁሉ፤ ቀንድ በዚህ ቦታ ብርታትን ያመለክታል። ሰበረ፤
ጠላት በተቃረበ ጊዜ፣
ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፤
በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳት፣
በያዕቆብ ላይ የእሳት ነበልባል ነደደ።
ד ዳሌት
4እንደ ጠላት ቀስቱን ገተረ፤
ቀኝ እጁ ተዘጋጅታለች፤
ለዐይን ደስ የሚያሰኙትን ሁሉ፤
እንደ ጠላት ዐረዳቸው፤
በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን ላይ፣
ቍጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።
ה ሄ
5ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፤
እስራኤልንም ዋጠ፤
ቤተ መንግሥቶቿን ሁሉ ዋጠ፤
ምሽጎቿን አፈራረሰ፤
በይሁዳ ሴት ልጅ፣
ልቅሶንና ሰቈቃን አበዛ።
ו ዋው
6ማደሪያውን እንደ አትክልት ስፍራ ባዶ አደረገ፤
መሰብሰቢያ ስፍራውን አፈረሰ፤
እግዚአብሔር ጽዮንን፣
ዓመት በዓላቶቿንና ሰንበታቷን እንድትረሳ አደረጋት፤
በጽኑ ቍጣው፣
ንጉሡንና ካህኑን እጅግ ናቀ።
ז ዛይን
7ጌታ መሠዊያውን ናቀ፤
መቅደሱንም ተወ፤
የቤተ መንግሥቶቿን ቅጥሮች፣
ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤
በዓመት በዓል ቀን እንደሚደረገው
በእግዚአብሔር ቤት በኀይል ጮኹ።
ח ኼት
8በጽዮን ሴት ልጅ ዙሪያ ያለውን ቅጥር፣
እግዚአብሔር ለማፍረስ ወሰነ፤
የመለኪያ ገመድ ዘረጋ፤
ከማጥፋትም እጆቹን አልሰበሰበም፤
ምሽጎችና ቅጥሮች እንዲያለቅሱ አደረገ፤
በአንድነትም ጠፉ።
ט ቴት
9በሮቿ ወደ ምድር ሰመጡ፤
የብረት መወርወሪያዎቻቸውን ሰባበረ፤ አጠፋቸውም፤
ንጉሧና መሳፍንቷ በአሕዛብ መካከል ተማርከው ተሰድደዋል፤
ሕጉ ከእንግዲህ አይኖርም፤
ነቢያቷም ከእንግዲህ፣
ከእግዚአብሔር ራእይ አያገኙም።
י ዮድ
10የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች፣
በምድር ላይ በዝምታ ተቀምጠዋል፤
በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ፤
ማቅም ለበሱ፤
የኢየሩሳሌም ወጣት ሴቶች፣
ራሳቸውን ወደ ምድር ዝቅ አደረጉ።
כ ካፍ
11ዐይኔ በልቅሶ ደከመ፤
ነፍሴ በውስጤ ተሠቃየች፤
ልቤም በሐዘን ፈሰሰች፣
በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣
ሕዝቤ ተደምስሰዋልና፤
ልጆችና ሕፃናት ደክመዋልና።
ל ላሜድ
12በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣
እንደ ቈሰሉ ሰዎች ሲደክሙ፣
በእናታቸው ክንድ ላይ፣
ነፍሳቸው በመውጣት ላይ ሳለች፣
“ምግብና የወይን ጠጅ የት አለ?”
እያሉ እናቶቻቸውን ይጠይቃሉ።
מ ሜም
13የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፤ ስላንቺ ምን ማለት እችላለሁ?
ከምንስ ጋራ አወዳድርሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፤
አጽናናሽ ዘንድ፣
በምን ልመስልሽ እችላለሁ?
ቍስልሽ እንደ ባሕር ጥልቅ ነው፤
ማንስ ሊፈውስሽ ይችላል?
נ ኑን
14የነቢያቶችሽ ራእይ፣
ሐሰትና ከንቱ ነው፤
ምርኮኛነትሽን ለማስቀረት፣
ኀጢአትሽን አይገልጡም።
የሚሰጡሽም የትንቢት ቃል፣
የሚያሳስትና ከመንገድ የሚያወጣ ነው።
ס ሳሜክ
15በአጠገብሽ የሚያልፉ ሁሉ፣
እጃቸውን ያጨበጭቡብሻል፤
“የውበት መደምደሚያ፣ የምድር ሁሉ ደስታ፣
የተባለች ከተማ ይህች ናትን?”
እያሉ ራሳቸውን በመነቅነቅ፣
በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያሾፋሉ።
ע ዐዪን
16ጠላቶችሽ ሁሉ በአንድ ላይ፣
አፋቸውን በኀይል ከፈቱ፤
ጥርሳቸውን እያፏጩ አሾፉ፤
እንዲህም አሉ፤ “ውጠናታል፤
የናፈቅነው ጊዜ ይህ ነበር፤
ኖረንም ልናየው በቃን።”
פ ፌ
17 እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤
ከረዥም ጊዜ በፊት የተናገረውን፣
ቃሉን ፈጸመ፤
ያለ ርኅራኄ አፈረሰሽ፤
ጠላት በሥቃይሽ ላይ እንዲደሰት፣
የጠላትሽንም ቀንድ#2፥17 ቀንድ በዚህ ቦታ ብርታትን ያመለክታል። ከፍ ከፍ አደረገ።
צ ጻዲ
18የሕዝቡ ልብ፣ ወደ ጌታ ጮኸ።
የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፤
ቀንና ሌሊት፣
እንባሽ እንደ ወንዝ ይፍሰስ፤
ለራስሽ ዕረፍትን አትስጪ፣
ዐይኖችሽ ከማንባት አያቋርጡ።
ק ቆፍ
19የሌሊቱ ሰዓት ሲጀምር፣
ተነሺ በሌሊት ጩኺ፤
በጌታ ፊት፣
ልብሽን እንደ ውሃ አፍስሺ፤
በየመንገዱ ዳር ላይ፣ በራብ ስለ ወደቁት፣
ስለ ልጆችሽ ሕይወት፣ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ።
ר ሬሽ
20“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እይ፤ ተመልከትም፤
በማን ላይ እንዲህ አድርገህ ታውቃለህ?
በውኑ እናቶች ሕፃኖቻቸውን፣
ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆች ይብሉን?
ካህኑና ነቢዩስ፣
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገደሉን?
ש ሲን እና ሺን
21“በየመንገዱ ዐቧራ ላይ፣
ወጣትና ሽማግሌ በአንድነት ወደቁ፤
ወይዛዝርቴና ጐበዛዝቴ፣
በሰይፍ ተገደሉ፤
በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤
ያለ ርኅራኄም ዐረድሃቸው።
ת ታው
22“በበዓል ቀን ለግብዣ እንደምትጠራ፣
ሽብርን ከየአቅጣጫው በእኔ ላይ ጠራህ፤
በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣
ማንም አላመለጠም ወይም አልተረፈም፤
የተንከባከብኋቸውንና ያሳደግኋቸውን፣
ጠላቴ አጠፋብኝ።”
Currently Selected:
ሰቈቃወ 2: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.