የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢያሱ 6

6
1በዚህ ጊዜ እስራኤላውያንን ከመፍራት የተነሣ፣ ኢያሪኮ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ ውጭ የሚወጣም ሆነ ወደ ውስጥ የሚገባ አልነበረም።
2 እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ኢያሪኮን ከንጉሥዋና ከተዋጊዎቿ ጋር አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻለሁ። 3ከተማዪቱን ከተዋጊዎቻችሁ ጋር አንድ ጊዜ ዙሩ፤ ይህንም ስድስት ቀን አድርጉ። 4ሰባት ካህናት፣ ሰባት ቀንደ መለከት ተሸክመው በታቦቱ ፊት ይውጡ፤ በሰባተኛውም ቀን ካህናቱ መለከት እየነፉ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ይዙሩ። 5የማያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ከፍ ያለ ጩኸት ያሰማ፤ ከዚያም የከተማዪቱ ቅጥር ይፈርሳል፤ ሕዝቡም ወደ ላይ ይወጣል፤ እያንዳንዱም ሰው በቀጥታ ይገባል።”
6ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባት ካህናትም ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው። 7ሕዝቡንም፣ “ወደ ፊት ሂዱ፤ ከተማዋን ዙሩ፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድመው ይሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ” ሲል አዘዛቸው።
8ኢያሱም ለሕዝቡ ከተናገረ በኋላ፣ ሰባቱ ካህናት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው መለከታቸውን እየነፉ ወደ ፊት ቀደሙ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተከተላቸው። 9የታጠቁ ተዋጊዎችም መለከት ከሚነፉት ካህናት ፊት ቀድመው ሲሄዱ፣ ደጀን የሆኑት ጠባቂዎች ደግሞ ታቦቱን ተከተሉ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ መለከቶቹ ባለማቋረጥ ይነፉ ነበር። 10ኢያሱ ሕዝቡን፣ “የማሸበሪያ ጩኸት አታሰሙ፤ ድምፃችሁ ከፍ ብሎ አይሰማ፤ ጩኹ እስከምላችሁም ቀን ድረስ ከአፋችሁ አንዲት ቃል አትውጣ፤ የምትጮኹት ከዚያ በኋላ ነው” ሲል አዘዛቸው።
11ስለዚህ ኢያሱ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው፣ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ እንዲዞሩ አደረገ። ከዚያም ሕዝቡ ወደ ሰፈር ተመልሰው ዐደሩ።
12ኢያሱ በማግስቱም ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። 13ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እየሄዱ፣ መለከቱን ባለማቋረጥ ይነፉ ጀመር፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም እነዚህን በመቅደም ሲሄዱ፣ የደጀን ጠባቂዎቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ታቦት ይከተሉ ነበር፤ ካህናቱም ሳያቋርጡ መለከት ይነፉ ነበር። 14በሁለተኛውም ቀን ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ከዞሩ በኋላ ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀን ሙሉም እንዲሁ አደረጉ።
15በሰባተኛው ቀን ገና ጎሕ ሲቀድ ተነሡ፤ እንደ በፊቱም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ የዞሯትም በዚያን ቀን ብቻ ነው። 16በሰባተኛው ዙር ላይ ካህናቱ መለከቱን ሲነፉ፣ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ሰጥቷችኋልና ጩኹ 17ከተማዪቱና በውስጧ ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ስለሆነ ፈጽማችሁ ዐጥፉ#6፥17 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው። እኛ የላክናቸውን ሰላዮች ስለ ሸሸገች ጋለሞታዪቱ#6፥17 በዚህም ሆነ በቍጥር 22 እና 25 ላይ፣ የእንግዳ ማረፊያ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። ረዓብ ብቻና ከእርሷ ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉት ሁሉ ይትረፉ። 18እናንተ ግን ዕርም ከሆኑት ነገሮች አንዳች በመውሰድ በራሳችሁ ላይ ጥፋት እንዳታመጡ እጃችሁን ሰብስቡ፤ ያለዚያ የእስራኤልን ሰፈር ለጥፋት ትዳርጋላችሁ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስበትም ታደርጋላችሁ፤ 19ብሩና ወርቁ እንዲሁም የናሱና የብረቱ ዕቃ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስለሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት ይግባ።”
20መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ፤ የመለከቱ ድምፅ ተሰምቶ፣ ሕዝቡ በኀይል ሲጮኽ ቅጥሩ ፈረሰ፤ እያንዳንዱም ሰው ሰተት ብሎ ገባ፤ ከተማዪቱም በእጃቸው ወደቀች። 21በከተማዪቱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፣ ማለትም ወንዱንና ሴቱን፣ ወጣቱንና ሽማግሌውን፣ ከብቱንና በጕን እንዲሁም አህያውን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።
22ኢያሱ ምድሪቱን የሰለሉትን ሁለቱን ሰዎች፣ “ወደ ጋለሞታዪቱ ቤት ሂዱ፤ በማላችሁላትም መሠረት እርሷንና የእርሷ የሆነውን ሁሉ ከዚያ አውጡ” አላቸው። 23ስለዚህ ሁለቱ ወጣት ሰላዮች ገብተው ረዓብን፣ አባቷንና እናቷን፣ ወንድሞቿንና የእርሷ የሆኑትን ሁሉ ከዚያ አወጧቸው። ቤተ ዘመዶቿንም ሁሉ አውጥተው ከእስራኤል ሰፈር ውጭ አስቀመጧቸው።
24ከዚያም ከተማዪቱን በሙሉ፣ በውስጧ ያለውንም ሁሉ አቃጠሉ፤ ብሩንና ወርቁን፣ የናሱንና የብረቱን ዕቃ ግን በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አኖሩ። 25ኢያሪኮን እንዲሰልሉ ኢያሱ የላካቸውን ሰዎች ስለ ደበቀች፣ ጋለሞታዪቱን ረዓብን፣ ቤተ ሰቧንና የእርሷ የሆኑትን ሁሉ አዳናቸው፤ እርሷም እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤላውያን መካከል ትኖራለች።
26በዚያን ጊዜም ኢያሱ፣ እንዲህ ሲል ማለ፤ “ይህችን ከተማ መልሶ የሚሠራት ሰው በእግዚአብሔር ፊት የተረገመ ይሁን፤
“መሠረቷን ሲጥል፣
የበኵር ልጁ ይጥፋ፤
ቅጥሮቿንም ሲያቆም፣
የመጨረሻ ልጁ ይጥፋ”
ብሎ ማለ።
27ስለዚህ እግዚአብሔር ከኢያሱ ጋር ነበር፤ ዝናውም በምድሪቱ ሁሉ ላይ ወጣ።

Currently Selected:

ኢያሱ 6: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ