ኢዮብ 8
8
በልዳዶስ
1ሹሐዊውም በልዳዶስ እንዲህ ሲል መለሰ፤
2“እንዲህ ያለውን ነገር የምትናገረው፣
ቃልህም እንደ ብርቱ ነፋስ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?
3እግዚአብሔር ፍትሕን ያጣምማልን?
ሁሉን ቻይ አምላክስ ጽድቅን ያጣምማልን?
4ልጆችህ በእርሱ ላይ ኀጢአት ሠርተው ከሆነ፣
ለኀጢአታቸው ቅጣት አሳልፎ ሰጥቷቸዋል።
5ነገር ግን አንተ ወደ እግዚአብሔር ብትመለከት፣
ሁሉን ቻይ አምላክን ብትማፀን፣
6ንጹሕና ቅን ብትሆን፣ እርሱ ስለ አንተ አሁኑኑ ይነሣል፤
ወደ ተገቢውም ስፍራህ ይመልስሃል።
7ጅማሬህ አነስተኛ ቢመስልም፣
ፍጻሜህ እጅግ ታላቅ ይሆናል።
8“የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፤
አባቶቻቸውም የደረሱበትን መርምረህ አግኝ፤
9እኛ ትናንት ስለ ተወለድን አንዳች አናውቅምና፤
ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው።
10እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፣
ከልቦናቸውም ቃልን የሚያወጡ አይደሉምን?
11ደንገል ረግረግ በሌለበት ስፍራ ይበቅላልን?
ቄጠማስ ውሃ በሌለበት ይለመልማልን?
12ገና በማደግ ላይ እያለ ሳይታጨድ፣
ከሌሎች ዕፀዋት ፈጥኖ ይደርቃል።
13እግዚአብሔርን የሚረሱ መጨረሻቸው እንዲህ ነው፤
አምላክ የለሽ ኑሮ የሚኖሩም ሁሉ ተስፋቸው ትጠፋለች።
14መተማመኛው ቀጭን ክር፣#8፥14 በዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም።
ድጋፉም የሸረሪት ድር ነው።
15ድሩ ላይ ቢደገፍ ይበጠስበታል፤
አጥብቆም ቢይዘው አይጸናም።
16ውሃ እንደ ጠገበ ተክል፣ ፀሓይ እየሞቀው፣
ቅርንጫፉን ሁሉ በአትክልቱ ስፍራ ላይ ይዘረጋል።
17ሥሩን በድንጋይ ክምር ላይ ይጠመጥማል፤
በዐለትም መካከል ስፍራ ያበጃል።
18ከስፍራው ሲወገድ ግን፣
ያ ቦታ ‘አይቼህ አላውቅም’ ብሎ ይክደዋል።
19እነሆ፤ ሕይወቱ በዚህ ያከትማል፤#8፥19 ወይም ያለው ደስታ ሁሉ
ሌሎች አትክልትም ከመሬት ይበቅላሉ።
20“እነሆ፤ እግዚአብሔር እንከን የሌለበትን ሰው አይጥልም፤
የክፉዎችንም እጅ አያበረታም፤
21እንደ ገና አፍህን በሣቅ፤
ከንፈሮችህንም በእልልታ ይሞላል።
22ጠላቶችህ ኀፍረት ይለብሳሉ፤
የክፉዎችም ድንኳን ይጠፋል።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.