ኢዮብም ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ከንቱ ሰው፣ ምን እመልስልሃለሁ? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ። አንድ ጊዜ ተናገርሁ፤ የምመልሰው የለኝም፤ ሁለተኛም ተናገርሁ፤ ከእንግዲህ አንዳች አልጨምርም።” እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ፣ ለኢዮብ መለሰለት፤ እንዲህም አለው፤ “እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እኔ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም መልስልኝ። “ፍርዴን ታቃልላለህን? ወይስ አንተ ጻድቅ ለመሆን እኔን ትኰንናለህ? እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ድምፅህስ እንደ እርሱ ድምፅ ሊያንጐደጕድ ይችላልን? እንግዲያስ ክብርንና ልዕልናን ተጐናጸፍ፤ ግርማ ሞገስንም ተላበስ፤ ቍጣህን አፍስስ፤ ትዕቢተኛውን ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው፤ ትዕቢተኛውን ሰው ሁሉ ተመልክተህ ዝቅ አድርገው፤ ክፉዎችንም በቆሙበት ስፍራ አድቅቃቸው። ሁሉንም በአንድ ላይ ከዐፈር ደባልቃቸው፤ ፊታቸውንም በመቃብር ውስጥ ሸፍን። እኔም ቀኝ እጅህ እንደምታድንህ፣ በዚያ ጊዜ አረጋግጬ እቀበላለሁ። “አንተን እንደ ፈጠርሁ፣ የፈጠርሁትን ‘ብሄሞት’ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል፤ ብርታቱ ወገቡ ውስጥ፣ ኀይሉም በሆዱ ጡንቻ ላይ ነው። ጅራቱ እንደ ጥድ ዛፍ ይወዛወዛል፤ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው። ዐጥንቱ እንደ ናስ ቱቦ፣ እጅና እግሮቹም እንደ ብረት ዘንግ ናቸው። እርሱ የእግዚአብሔር ሥራ አውራ ነው፤ በሰይፍ ሊቀርበውም የሚችል ፈጣሪው ብቻ ነው። ኰረብቶች ምግቡን ያበቅሉለታል፤ አውሬዎችም ሁሉ በዙሪያው ይፈነጫሉ። በውሃ ላይ በሚያድጉ ዕፀዋት ጥላ ሥር ይተኛል፤ በረግረግ ስፍራ ደንገል መካከል ይደበቃል። በውሃ ላይ የሚያድጉ ዕፀዋት በጥላቸው ይጋርዱታል፤ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይሸፍኑታል። ወንዙ በኀይል ቢጐርፍም፣ አይደነግጥም፤ ዮርዳኖስ እስከ አፉ ቢሞላም፣ እርሱ ተረጋግቶ ይቀመጣል። ዐይኑን ሸፍነህ ልትይዘው፣ አጥምደህም አፍንጫውን ልትበሳ ትችላለህ?
ኢዮብ 40 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢዮብ 40
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢዮብ 40:3-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos