የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢዮብ 31

31
1“ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣
ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።
2ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሰው ዕድል ፈንታው፣
ከአርያም ሁሉን ከሚችል አምላክስ ዘንድ ቅርሱ ምንድን ነው?
3ለኀጢአተኞች ጥፋት፣
ክፉ ለሚያደርጉም መቅሠፍት አይደለምን?
4እርሱ መንገዴን አያይምን?
ርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?
5“በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ፣
እግሬም ወደ ሽንገላ ቸኵሎ ከሆነ፣
6እግዚአብሔር በእውነተኛ ሚዛን ይመዝነኝ፤
ነውር እንደሌለብኝም ይወቅ።
7አረማመዴ ከመንገድ ወጣ ብሎ፣
ልቤ ዐይኔን ተከትሎ፣
ወይም እጄ ረክሶ ከሆነ፣
8የዘራሁትን ሌላ ይብላው፤
ሰብሌም ተነቅሎ ይጥፋ።
9“ልቤ ሌላዋን ሴት ከጅሎ፣
በባልንጀራዬ ደጅ አድብቼ ከሆነ፣
10ሚስቴ የሌላ ሰው እህል ትፍጭ፤
ሌሎች ሰዎችም ይተኟት፤
11ይህ አሳፋሪ፣
ፍርድም የሚገባው ኀጢአት ነውና።
12ይህ የሚያቃጥልና የሚያጠፋ#31፥12 ዕብራይስጡ አባዶን ይላል። እሳት ነው፤
ቡቃያዬንም ባወደመ ነበር።
13“ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቼ አቤቱታ ባቀረቡ ጊዜ፣
ፍርድ አዛብቼ ከሆነ፣
14እግዚአብሔር ሲነሣ ምን አደርጋለሁ?
ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ?
15እኔን በማሕፀን ውስጥ የፈጠረኝ እነርሱን የፈጠረ አይደለምን?
በሆድ ውስጥ የሠራንስ እርሱ ራሱ አይደለምን?
16“ለድኻ የሚያስፈልገውን ከልክዬ ከሆነ፣
ወይም የመበለቲቱን ዐይን አፍዝዤ ከሆነ፣
17እንጀራዬን ከድኻ ዐደጉ ጋር ሳልካፈል፣
ለብቻዬ በልቼ ከሆነ፣
18ይልቁን ድኻ ዐደጉን ከታናሽነቴ ጀምሮ እንደ አባት አሳደግሁት፤
መበለቲቱንም ከተወለድሁ ጀምሮ መንገድ መራኋት፤
19በልብስ ዕጦት ሰው ሲጠፋ፣
ወይም ዕርቃኑን ያልሸፈነ ድኻ አይቼ፣
20በበጎቼ ጠጕር ስላሞቅሁት፣
ልቡ ባርኮኝ ካልሆነ፣
21በአደባባይ ተሰሚነት አለኝ ብዬ፣
በድኻ ዐደጉ ላይ እጄን አንሥቼ ከሆነ፣
22ትከሻዬ ከመጋጠሚያው ይነቀል፤
ክንዴም ከመታጠፊያው ይሰበር፤
23የእግዚአብሔርን ቍጣ በመፍራቴ፣
እንዲህ ያሉ ነገሮች መፈጸም አልቻልሁም።
24“ወርቅን ተስፋ አድርጌ፣
ወይም ንጹሑን ወርቅ፣ ‘አንተ መታመኛዬ ነህ’ ብዬ ከሆነ፣
25እጄ ባገኘችው ሀብት፣
በባለጠግነቴም ብዛት ደስ ብሎኝ ከሆነ፣
26የፀሓይን ድምቀት አይቼ፣
ወይም የጨረቃን አካሄድ ግርማ ተመልክቼ፣
27ልቤ በስውር ተታልሎ፣
ስለ ክብራቸው አፌ እጄን ስሞ ከሆነ፣
28ለልዑል እግዚአብሔር ታማኝ አለመሆኔ ነውና፣
ይህም ደግሞ የሚያስቀጣኝ በደል በሆነ ነበር።
29“በጠላቴ ውድቀት ደስ ብሎኝ፣
በደረሰበትም መከራ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፣
30እኔ ግን በነፍሱ ላይ ክፉ እንዲመጣ በመራገም፣
አንደበቴን ለኀጢአት ከቶ አሳልፌ አልሰጠሁም።
31የቤቴ ሰዎች፣ ‘ከኢዮብ ከብት ሥጋ አስቈርጦ፣
ያልጠገበ ማን ነው?’ ብለው ካልሆነ፣
32ነገር ግን ቤቴ ለመንገደኛው ዘወትር ክፍት ስለ ነበር፣
መጻተኛው በጐዳና ላይ አያድርም ነበር።
33ሰዎች#31፥33 ወይም አዳም እንዳደረገው እንደሚያደርጉት በደሌን በልቤ በመሰወር፣
ኀጢአቴን ሸሽጌ ከሆነ፣
34ሕዝቡን በመፍራት፣
የወገኖቼንም ንቀት በመሸሽ፣
ወደ ደጅ ሳልወጣ፣ ዝም ብዬ ቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም።
35“ምነው የሚሰማኝ ባገኝ!
የመከላከያ ፊርማዬ እነሆ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፤
ከሳሼም ክሱን በጽሑፍ ያቅርብ።
36በርግጥ ትከሻዬ ላይ በደረብሁት፣
እንደ አክሊልም ራሴ ላይ በደፋሁት ነበር።
37እያንዳንዱን ርምጃዬን በገለጽሁለት፣
እንደ ልዑል እየተንጐራደድሁ በቀረብሁት ነበር።
38“ዕርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ ከሆነ፣
ትልሞቿ ሁሉ በእንባ ርሰው እንደ ሆነ፣
39ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፣
የባለመሬቶቿን ነፍስ አሳዝኜ ከሆነ፣
40በስንዴ ፈንታ እሾኽ፣
በገብስም ምትክ ዐረም ይብቀልብኝ።”
የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።

Currently Selected:

ኢዮብ 31: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ