“ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሰው ዕድል ፈንታው፣ ከአርያም ከሁሉን ቻይ አምላክስ ዘንድ ቅርሱ ምንድን ነው? ለኀጢአተኞች ጥፋት፣ ክፉ ለሚያደርጉም መቅሠፍት አይደለምን? እርሱ መንገዴን አያይምን? ርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን? “በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ፣ እግሬም ወደ ሽንገላ ቸኵሎ ከሆነ፣ እግዚአብሔር በጽድቅ ሚዛን ይመዝነኝ፤ ነውር እንደሌለብኝም ይወቅ። አረማመዴ ከመንገድ ወጣ ብሎ፣ ልቤ ዐይኔን ተከትሎ፣ ወይም እጄ ረክሶ ከሆነ፣ የዘራሁትን ሌላ ይብላው፤ ሰብሌም ተነቅሎ ይጥፋ። “ልቤ ሌላዋን ሴት ከጅሎ፣ በባልንጀራዬ ደጅ አድብቼ ከሆነ፣ ሚስቴ የሌላ ሰው እህል ትፍጭ፤ ሌሎች ሰዎችም ይተኟት፤ ይህ አሳፋሪ፣ ፍርድም የሚገባው ኀጢአት ነውና። ይህ የሚያቃጥልና የሚያጠፋ እሳት ነው፤ ቡቃያዬንም ባወደመ ነበር። “ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቼ አቤቱታ ባቀረቡ ጊዜ፣ ፍርድ አዛብቼ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ሲነሣ ምን አደርጋለሁ? ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ? እኔን በማሕፀን ውስጥ የፈጠረኝ እነርሱን የፈጠረ አይደለምን? በሆድ ውስጥ የሠራንስ እርሱ ራሱ አይደለምን? “ለድኻ የሚያስፈልገውን ከልክዬ ከሆነ፣ ወይም የመበለቲቱን ዐይን አፍዝዤ ከሆነ፣ እንጀራዬን ከድኻ አደጉ ጋራ ሳልካፈል፣ ለብቻዬ በልቼ ከሆነ፣ ይልቁን ድኻ አደጉን ከታናሽነቴ ጀምሮ እንደ አባት አሳደግሁት፤ መበለቲቱንም ከተወለድሁ ጀምሮ መንገድ መራኋት፤ በልብስ ዕጦት ሰው ሲጠፋ፣ ወይም ዕርቃኑን ያልሸፈነ ድኻ አይቼ፣ በበጎቼ ጠጕር ስላሞቅሁት፣ ልቡ ባርኮኝ ካልሆነ፣ በአደባባይ ተሰሚነት አለኝ ብዬ፣ በድኻ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ ከሆነ፣ ትከሻዬ ከመጋጠሚያው ይነቀል፤ ክንዴም ከመታጠፊያው ይሰበር፤ የእግዚአብሔርን ቍጣ በመፍራቴ፣ እንዲህ ያሉ ነገሮች መፈጸም አልቻልሁም። “ወርቅን ተስፋ አድርጌ፣ ወይም ንጹሑን ወርቅ፣ ‘አንተ መታመኛዬ ነህ’ ብዬ ከሆነ፣ እጄ ባገኘችው ሀብት፣ በባለጠግነቴም ብዛት ደስ ብሎኝ ከሆነ፣ የፀሓይን ድምቀት አይቼ፣ ወይም የጨረቃን አካሄድ ግርማ ተመልክቼ፣ ልቤ በስውር ተታልሎ፣ ስለ ክብራቸው አፌ እጄን ስሞ ከሆነ፣ ለልዑል እግዚአብሔር ታማኝ አለመሆኔ ነውና፣ ይህም ደግሞ የሚያስቀጣኝ በደል በሆነ ነበር። “በጠላቴ ውድቀት ደስ ብሎኝ፣ በደረሰበትም መከራ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፣ እኔ ግን በነፍሱ ላይ ክፉ እንዲመጣ በመራገም፣ አንደበቴን ለኀጢአት ከቶ አሳልፌ አልሰጠሁም። የቤቴ ሰዎች፣ ‘ከኢዮብ ከብት ሥጋ አስቈርጦ፣ ያልጠገበ ማን ነው?’ ብለው ካልሆነ፣ ነገር ግን ቤቴ ለመንገደኛው ዘወትር ክፍት ስለ ነበር፣ መጻተኛው በጐዳና ላይ አያድርም ነበር። ሰዎች እንደሚያደርጉት በደሌን በልቤ በመሰወር፣ ኀጢአቴን ሸሽጌ ከሆነ፣ ሕዝቡን በመፍራት፣ የወገኖቼንም ንቀት በመሸሽ፣ ወደ ደጅ ሳልወጣ፣ ዝም ብዬ ቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። “ምነው የሚሰማኝ ባገኝ! የመከላከያ ፊርማዬ እነሆ፤ ሁሉን ቻይ አምላክ ይመልስልኝ፤ ከሳሼም ክሱን በጽሑፍ ያቅርብ።
ኢዮብ 31 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢዮብ 31
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢዮብ 31:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች