ኢዮብ 21
21
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤
2“ቃሌን በጥንቃቄ ስሙ፤
የምታጽናኑኝም በዚህ ይሁን፤
3ንግግሬን በትዕግሥት አድምጡ፤
ከተናገርሁ በኋላ፣ መሣለቅ ትችላላችሁ።
4“በውኑ ቅርታዬ በሰው ላይ ነውን?
ትዕግሥት ማጣትስ አይገባኝምን?
5ተመልከቱኝና ተገረሙ፤
አፋችሁን በእጃችሁ ለጕሙ።
6ስለዚህ ነገር ባሰብሁ ቍጥር እደነግጣለሁ፤
ሰውነቴም በፍርሀት ይንቀጠቀጣል።
7ኀጢአተኞች ለምን በሕይወት ይኖራሉ?
ለምን ለእርጅና ይበቃሉ? ለምንስ እያየሉ ይሄዳሉ?
8ዘራቸው በዐይናቸው ፊት፣
ልጆቻቸውም በዙሪያቸው ጸንተው ሲኖሩ ያያሉ፤
9ቤታቸው ያለ ሥጋት በሰላም ይኖራል፤
የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።
10ኮርማቸው ዘሩ በከንቱ አይወድቅም፤
ያስረግዛል፤ ላማቸውም ሳትጨነግፍ ትወልዳለች።
11ልጆቻቸውን እንደ በግ መንጋ ያሰማራሉ፤
ሕፃናታቸውም ይቦርቃሉ።
12በከበሮና በክራር ይዘፍናሉ፤
በዋሽንትም ድምፅ ይፈነጫሉ።
13ዕድሜያቸውን በተድላ ያሳልፋሉ፤
በሰላምም#21፥13 ወይም በፍጥነት ማለት ነው። ወደ መቃብር#21፥13 በዕብራይስጡ፣ ሲኦል ይላል። ይወርዳሉ።
14እግዚአብሔርንም እንዲህ ይሉታል፤ ‘አትድረስብን!
መንገድህንም ማወቅ አንፈልግም።
15እናገለግለው ዘንድ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ ማን ነው?
ወደ እርሱ ብንጸልይስ ምን እናገኛለን?’
16ይሁንና ብልጽግናቸው በእጃቸው አይደለም፤
ከኀጢአተኞች ምክር እርቃለሁ።
17“የኀጢአተኞች መብራት የጠፋው ስንት ጊዜ ነው?
የእግዚአብሔር ቍጣ መከራ የመጣባቸው፣
መቅሠፍትም የደረሰባቸው ስንት ጊዜ ነው?
18በነፋስ ፊት እንዳለ ገለባ፣
በዐውሎ ነፋስም እንደ ተወሰደ ዕብቅ የሆኑት ስንት ጊዜ ነው?
19እናንተ፣ ‘እግዚአብሔር የሰውን ቅጣት ለልጆቹ ያከማቻል’ ትላላችሁ፤
ነገር ግን ያውቀው ዘንድ ለሰውየው ለራሱ ይክፈለው፤
20ዐይኖቹ የራሱን ውድቀት ይዩ፤
ሁሉን ከሚችል አምላክ#21፥17-20 17፡18 ቃለ አጋኖዎች ሲሆኑ፣ 19፡20 ደግሞ ብያኔዎች ናቸው። ቍጣ ይጠጣ።
21ሰው ወራቱ በተገባደደ ጊዜ፣
ለቀሪ ቤተ ሰቡ ምን ይገድደዋል?
22“ከፍ ባሉት ላይ ለሚፈርድ አምላክ፣
ዕውቀትን ሊያስተምረው የሚችል አለን?
23አንድ ሰው በፍጹም ተድላ ደስታ እየኖረ፣
በሙሉ ብርታቱም እያለ ይሞታል፤
24ሰውነቱ#21፥24 የዚህ ቃል የዕብራይስጡ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። በምቾት፣
ዐጥንቱም በሥብ ተሞልቶ እያለ በሞት ይለያል።
25ሌላው ሰው ደግሞ አንዳች መልካም ነገር ሳያይ፣
በተመረረች ነፍስ ይሞታል፤
26ሁለቱም በዐፈር ውስጥ አንድ ላይ ይተኛሉ፤
ትልም ይወርሳቸዋል።
27“እነሆ፣ ምክራችሁን፣
በእኔ ላይ ያሤራችሁትንም ተረድቻለሁ።
28እናንተ፣ ‘የትልቁ ሰው ቤት፣
ኀጢአተኛውም የኖረበት ድንኳን የት አለ?’ አላችሁ፤
29መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን?
የነገሯችሁንስ ነገር በጥሞና አላዳመጣችሁምን?
30ክፉ ሰው በመቅሠፍት ቀን እንደሚጠበቅ፣
በቍጣም ቀን እንደሚተርፍ#21፥30 ወይም ለመቅሠፍት ቀን ተጠብቆ እንደሚቈይ ማለት ነው። አታውቁምን?
31ተግባሩን ፊት ለፊት የሚነግረው ማን ነው?
የእጁንስ ማን ይሰጠዋል?
32ወደ መቃብር ይወስዱታል፤
ለመቃብሩም ጠባቂ ይደረግለታል።
33የሸለቈው ዐፈር ምቹ ይሆንለታል፤
ሰው ሁሉ ይከተለዋል፤
ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝብ#21፥33 ወይም ስፍር ቍጥር እንደ ሌለው ሕዝብ ማለት ነው። በፊቱ ይሄዳል።
34“መልሳችሁ ከሐሰት በስተቀር ሌላ አይገኝበትም!
ታዲያ፣ በማይረባ ነገር እንዴት ልታጽናኑኝ ትችላላችሁ?”
Currently Selected:
ኢዮብ 21: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.