የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 9:18-41

ዮሐንስ 9:18-41 NASV

አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዴት ማየት እንደ ቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኵራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ። ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ” አለ። እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ። ከዚህ በኋላ በእርሱ ላይ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ አሉት፤ “የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን! እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ እንኳ አናውቅም።” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚያስደንቅ ነው፤ ይሁን እንጂ እርሱ ዐይኖቼን ከፈተልኝ። እግዚአብሔር የሚሰማው፣ የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እንጂ፣ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።” እነርሱም፣ “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” ሲሉ መለሱለት፤ አባረሩትም። ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁንም ከአንተ ጋር የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም፣ “ዕውሮች እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው፣ “ምን ማለትህ ነው? ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።

Free Reading Plans and Devotionals related to ዮሐንስ 9:18-41