ኢየሱስም እንደ ገና፣ “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ በኀጢአታችሁም ትሞታላችሁ፤ እኔ ወደምሄድበት ግን ልትመጡ አትችሉም” አላቸው። አይሁድም፣ “ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ ያለው ራሱን ሊገድል ይሆን?” አሉ። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። በኀጢአታችሁ እንደምትሞቱ ነግሬአችኋለሁ፤ እኔ እርሱ ነኝ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደ ሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና።” እነርሱም፣ “ለመሆኑ፣ አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እስካሁን የነገርኋችሁ እኔ እርሱ ነኝ፤ በእናንተ ላይ ብዙ የምናገረውና ብዙ የምፈርደው ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ ታማኝ ነው፤ ከርሱም የሰማሁትን ለዓለም እናገራለሁ።” እነርሱም ስለ አብ እየነገራቸው እንደ ነበር አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰው ልጅን ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ፣ ያ ያልሁት እርሱ እኔ እንደ ሆንሁና አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ፤ የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋራ ነው፤ ምን ጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።” ይህንም እንደ ተናገረ ብዙዎች በርሱ አመኑ። ኢየሱስም በርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።” እነርሱም መልሰው፣ “እኛ የአብርሃም ልጆች ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ፣ ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ኀጢአት የሚያደርግ የኀጢአት ባሪያ ነው፤ ባሪያ ለዘለቄታ በቤተ ሰቡ ውስጥ አይኖርም፤ ልጅ ግን ምን ጊዜም በቤት ይኖራል። እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ።
ዮሐንስ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 8:21-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች