ዮሐንስ 7:1-32

ዮሐንስ 7:1-32 NASV

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፣ በዚያ የነበሩት አይሁድ ሊገድሉት ስለ ፈለጉ፣ በይሁዳ አውራጃ መዘዋወር ትቶ በገሊላ ተዘዋወረ። የአይሁድ የዳስ በዓል በተቃረበ ጊዜ ግን፣ የኢየሱስ ወንድሞች እንዲህ አሉት፤ “ደቀ መዛሙርትህም ደግሞ የምታደርገውን ታምራት እንዲያዩ፣ ከዚህ ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱን ሊገልጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ ማንም የለምና። አንተም እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ፣ ራስህን ለዓለም ግለጥ።” የገዛ ወንድሞቹ እንኳ አላመኑበትም ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ገና አልደረሰም፤ ለእናንተ ግን ማንኛውም ጊዜ ምቹ ነው። ዓለም እናንተን ሊጠላ አይችልም፤ እኔ ግን፣ አድራጎቱ ክፉ መሆኑን ስለምመሰክርበት ይጠላኛል። እናንተ ወደ በዓሉ ሂዱ፤ ለእኔ ትክክለኛው ጊዜ ስላልደረሰ ወደ በዓሉ አልሄድም።” ይህን ብሏቸው በገሊላ ቈየ። ይሁን እንጂ፣ ወንድሞቹ ወደ በዓሉ ከሄዱ በኋላ፣ እርሱም በግልጽ ሳይሆን በስውር ወደ በዓሉ ሄደ። በበዓሉም ላይ አይሁድ፣ “ያ ሰው የት አለ?” እያሉ ይፈልጉት ነበር። ስለ እርሱ በሕዝቡ መካከል ብዙ ጕምጕምታ ነበር። አንዳንዶች፣ “ደግ ሰው ነው” አሉ። ሌሎች ግን፣ “የለም፤ ሕዝቡን የሚያስት ነው” አሉ። ይሁን እንጂ አይሁድን ከመፍራት የተነሣ ስለ እርሱ በግልጽ የተናገረ ማንም አልነበረም። በበዓሉም አጋማሽ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ጀመር። አይሁድም በመደነቅ፣ “ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ሊያውቅ ቻለ?” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው። ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ፣ የእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል፤ ከራሱ የሚናገር፣ ያን የሚያደርገው ለራሱ ክብርን ስለሚሻ ነው፤ ስለ ላከው ክብር የሚሠራ ግን እርሱ እውነተኛ ነው፤ ሐሰትም አይገኝበትም። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ነገር ግን አንዳችሁም ሕጉን አልጠበቃችሁም። ለምን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?” ሕዝቡም፣ “አንት ጋኔን ያደረብህ! ደግሞ አንተን ማን ሊገድል ይፈልጋል?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሥራ ብሠራ፣ ሁላችሁም ተገረማችሁ። ግዝረት የመጣው ከአባቶች እንጂ ከሙሴ አይደለም፤ ሆኖም ሙሴ ግዝረትን ስለ ሰጣችሁ፣ በሰንበት እንኳ ሕፃን ትገርዛላችሁ። የሙሴ ሕግ እንዳይሻር ሕፃን በሰንበት የሚገረዝ ከሆነ፣ የሰውን ሁለንተና በሰንበት ስለ ፈወስሁ ለምን በእኔ ላይ ትቈጣላችሁ? የሰውን ፊት በማየት መፍረድ ትታችሁ ቅን ፍርድ ፍረዱ።” በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ አሉ፤ “ሊገድሉት የሚፈልጉት ሰው ይህ አይደለምን? ይኸው እርሱ በአደባባይ ይናገራል፤ አንድም ቃል አይናገሩትም፤ ክርስቶስ ነው ብለው ባለሥልጣኖቹም ተቀብለውት ይሆን? ይህ ሰው ግን ከየት እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን፤ ክርስቶስ ሲመጣ እኮ ከየት እንደ ሆነ ማንም አያውቅም።” ኢየሱስ በቤተ መቅደስ አደባባይ ሲያስተምር ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “አዎን፣ እኔን ታውቁኛላችሁ፤ ከየት እንደ ሆንሁም ታውቃላችሁ። እኔ እዚህ ያለሁት በገዛ ራሴ አይደለም፤ ነገር ግን የላከኝ እርሱ እውነተኛ ነው። እናንተ አታውቁትም፤ እኔ ግን ከርሱ ዘንድ ስለ ሆንሁ፣ እርሱም ስለ ላከኝ ዐውቀዋለሁ።” ስለዚህ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አላሳረፈበትም፤ ሆኖም ከሕዝቡ ብዙዎች በርሱ አምነው፣ “ታዲያ፣ ክርስቶስ ሲመጣ ይህ ሰው ከሚሠራቸው ታምራዊ ምልክቶች የበለጠ ያደርጋል?” አሉ። ፈሪሳውያን፣ ሕዝቡ ስለ እርሱ በጕምጕምታ የሚነጋገረውን ነገር ሰሙ፤ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም እንዲይዙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችን ላኳቸው።