የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 5:19-29

ዮሐንስ 5:19-29 NASV

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ እንጂ ወልድ ከራሱ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ያደርጋልና፤ አብ ወልድን ስለሚወድድ የሚያደርገውን ሁሉ ያሳየዋል፤ ትደነቁም ዘንድ ከእነዚህም የሚበልጥ ነገር ያሳየዋል። ምክንያቱም አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል። አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ይኸውም፣ ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩት ዘንድ ነው፤ ወልድን የማያከብር፣ የላከውን አብንም አያከብርም። “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤ ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።