አንዲት ሳምራዊት ሴት ውሃ ለመቅዳት ስትመጣ ኢየሱስ፣ “እባክሽ የምጠጣው ስጪኝ” አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር። ሳምራዊቷም፣ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ፣ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ትላለህ?” አለችው፤ ይህን ማለቷ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስለማይተባበሩ ነው። ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት። ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ መቅጃ የለህም፤ ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ ይህን የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? ለመሆኑ አንተ፣ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን፣ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱ ራሱና ልጆቹ፣ እንስሳቱም ከዚሁ ጕድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።” ሴትዮዋም፣ “ጌታዬ፤ እንዳልጠማና ውሃ ለመቅዳት እንዳልመላለስ፣ እባክህ ይህን ውሃ ስጠኝ” አለችው። እርሱም፣ “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ተመለሽ” አላት። ሴትዮዋም፣ “ባል የለኝም” ብላ መለሰች። ኢየሱስም፣ እንዲህ አላት፤ “ባል የለኝም ማለትሽ ትክክል ነው፤ በርግጥ አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለውም ባልሽ ስላልሆነ፣ የተናገርሽው እውነት ነው።” ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ፤ አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ አይሁድ ግን ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “አንቺ ሴት፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ። እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለሆነ ለምናውቀው እንሰግዳለን። በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።” ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው። ኢየሱስም፣ “የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገልጦ ነገራት። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር በማግኘታቸው ተደነቁ፤ ሆኖም ግን፤ “ምን ፈለግህ?” ወይም፣ “ከእርሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም። ሴትዮዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ለሕዝቡም፣ “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እርሱ ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” አለች፤
ዮሐንስ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 4:7-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos