የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 4:46-54

ዮሐንስ 4:46-54 NASV

ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገበት፣ በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ ዳግመኛ መጣ፤ በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ፤ ይህም ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እርሱ ሄደና በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ልጁን መጥቶ እንዲፈውስለት ለመነው። ኢየሱስም፣ “መቼውንም እናንተ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ካላያችሁ አታምኑም” አለው። ሹሙም፣ “ጌታዬ፤ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ድረስልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራልና ሂድ” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ፤ በመንገድ ላይ እንዳለም፣ ባሮቹ አግኝተውት ልጁ በሕይወት መኖሩን ነገሩት። እርሱም ልጁ በስንት ሰዓት እንደ ተሻለው ሲጠይቃቸው፣ “ትኵሳቱ የለቀቀው ትናንት በሰባት ሰዓት ላይ ነው” አሉት። አባትየውም ሰዓቱ ኢየሱስ፣ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለበት ሰዓት መሆኑን ተገነዘበ፤ እርሱና ቤተ ሰቡም ሁሉ አመኑ። ይህም፣ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ታምራዊ ምልክት ነው።