የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዮሐንስ 2:1-11

ዮሐንስ 2:1-11 NASV

በሦስተኛው ቀን፣ በገሊላ አውራጃ፣ በቃና ከተማ ሰርግ ነበር፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር። የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜም የኢየሱስ እናት፣ “የወይን ጠጅ እኮ ዐለቀባቸው” አለችው። ኢየሱስም፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ምን አድርግ ትይኛለሽ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት። እናቱም በዚያ የነበሩትን አገልጋዮች፣ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው። በአይሁድ የመንጻት ሥርዐት መሠረት፣ ከሰባ አምስት እስከ አንድ መቶ ዐሥራ አምስት ሊትር የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት ጋኖች በዚያ ነበሩ። ኢየሱስ አገልጋዮቹን፣ “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” አላቸው፤ እነርሱም፣ ጋኖቹን እስከ አፋቸው ሞሏቸው። እርሱም፣ “ከላዩ ቀድታችሁ ለድግሱ ኀላፊ ስጡት” አላቸው። እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ። የድግሱ ኀላፊም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። እርሱም ሙሽራውን ለብቻው ጠርቶ፣ “ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” አለው። ኢየሱስም ይህን የታምራዊ ምልክቶቹ መጀመሪያ በገሊላ አውራጃ በቃና ከተማ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።

Free Reading Plans and Devotionals related to ዮሐንስ 2:1-11