ዮሐንስ 16:1-15

ዮሐንስ 16:1-15 NASV

“ይህን ሁሉ የነገርኋችሁ እንዳትሰናከሉ ነው። ከምኵራብ ያስወጧችኋል፤ እንዲያውም የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንዳገለገለ የሚቈጥርበት ጊዜ ይመጣል። ይህን ሁሉ የሚያደርጉባችሁ፣ አብን ወይም እኔን ስላላወቁ ነው። አስቀድሜ ይህን የነገርኋችሁ ጊዜው ሲደርስ እንድታስታውሱ ነው፤ ከእናንተ ጋራ ስለ ነበርሁ፣ ይህን ከመጀመሪያው አልነገርኋችሁም። “እንግዲህ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ይሁን እንጂ ከእናንተ፣ ‘የምትሄደው የት ነው?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። ይህን በመናገሬም ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል፤ ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ በሚመጣበትም ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሣል። ስለ ኀጢአት ሲባል፣ ሰዎች በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅ፣ ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም፣ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። “ብዙ የምነግራችሁ ነበረኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።