ኤርምያስ 49
49
ስለ አሞን የተነገረ መልእክት
1ስለ አሞናውያን፤
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እስራኤል ወንዶች ልጆች አልወለደምን?
ወራሾችስ የሉትምን?
ታዲያ፣ ሚልኮም#49፥1 ወይም ንጉሣቸው፤ ዕብራይስጡ መልካም ይላል፤ 3 ይመ። ጋድን ለምን ወረሰ?
የርሱ ሰዎች ለምን በከተሞቿ ይኖራሉ?
2ስለዚህ በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ፣
የጦርነት ውካታ ድምፅ
የሚሰማበት ጊዜ ይመጣል፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
“እርሷም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤
በዙሪያዋ ያሉት መንደሮችም ይቃጠላሉ፤
እስራኤልም ከአገሯ ያስወጧትን፣
ከአገሯ ታስወጣለች፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
3“ሐሴቦን ሆይ፤ ጋይ ጠፍታለችና ዋይ በይ፤
የረባት ሴቶች ልጆች ሆይ ጩኹ፤
ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ፤
ሚልኮም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋራ፣
ተማርኮ ይወሰዳልና፣
በቅጥር ውስጥ ወዲያ ወዲህ ተሯሯጡ።
4አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤
በሸለቆችሽ ለምን ትመኪያለሽ?
ለምንስ በፍሬያማ ሸለቆሽ ትኵራሪያለሽ?
በብልጽግናሽ ተማምነሽ፣
‘ማን ሊነካኝ ይችላል?’ ትያለሽ።
5በዙሪያሽ ካሉት ሁሉ ዘንድ፣
ሽብር አመጣብሻለሁ፤”
ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤
“እያንዳንዳችሁ ትሰደዳላችሁ፤
በሽሽት ላይ ያሉትንም የሚሰበስብ አይገኝም።
6“ከዚያ በኋላ ግን፣ የአሞናውያንን ምርኮ እመልሳለሁ”
ይላል እግዚአብሔር።
ስለ ኤዶም የተነገረ መልእክት
49፥9-10 ተጓ ምብ – አብ 5-6
49፥14-16 ተጓ ምብ – አብ 1-4
7ስለ ኤዶም፤
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ጥበብ ከቴማን ጠፍቷልን?
ምክር ከአስተዋዮች ርቋልን?
ጥበባቸውስ ተሟጧልን?
8ዔሳውን በምቀጣ ጊዜ፣
ጥፋት ስለማመጣበት፣
እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ፤
ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ሽሹ፤ ጥልቅ ጕድጓድ ውስጥ ተደበቁ።
9ወይን ለቃሚዎች ወደ አንተ ቢመጡ፣
ጥቂት ወይን አያስቀሩምን?
ሌቦችስ በሌሊት ቢመጡ፣
የሚሰርቁት የሚፈልጉትን ብቻ አይደለምን?
10እኔ ግን ዔሳውን አራቍተዋለሁ፤
መደበቅም እንዳይችል፣
መሸሸጊያ ስፍራዎቹን እገልጣለሁ፤
ልጆቹ፣ ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ ይጠፋሉ፤
እርሱም ራሱ አይኖርም።
11ወላጆች የሌላቸውን ልጆችህን ተዋቸው፤ እኔ ለሕይወታቸው እጠነቀቃለሁ፤ መበለቶቻችሁም በእኔ ይታመኑ።”
12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከጽዋው መጠጣት የማይገባቸው ሊጠጡ ግድ ከሆነ፣ አንተ እንዴት ሳትቀጣ ትቀራለህ? መቀጣትህ አይቀርም፤ መጠጣት ይገባሃል። 13ባሶራ ፈራርሳ የድንጋጤ፣ የመዘባበቻና የርግማን ምልክት እንደምትሆን በራሴ ምያለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከተሞቿም ሁሉ ለዘላለም ባድማ ይሆናሉ።”
14 ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት ሰምቻለሁ፤
“እርሷን ለመውጋት ተሰብሰቡ፤
ለጦርነትም ውጡ”
የሚል መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኳል።
15“እነሆ፤ በአሕዛብ መካከል ታናሽ፣
በሰው ልጆችም ዘንድ የተናቅህ አደርግሃለሁ።
16አንተ በዐለት ንቃቃት ውስጥ የምትኖር፣
የተራራውንም ከፍታ የያዝህ ሆይ፤
የምትነዛው ሽብር፣
የልብህም ኵራት አታልሎሃል፤
መኖሪያህን እስከ ንስር ከፍታ ቦታ ብትሠራም፣
ከዚያ ወደ ታች አወርድሃለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር።
17“ኤዶም የድንጋጤ ምልክት ትሆናለች፤
ከቍስሎቿም ሁሉ የተነሣ፣
በዚያም የሚያልፉ ሁሉ ወይ ጉድ! ይላሉ።
18በዙሪያቸው ካሉት ከተሞች ጋራ፣
ሰዶምና ገሞራ እንደ ተገለበጡ፣”
ይላል እግዚአብሔር፤
“እንዲሁ ማንም በዚያ አይኖርም፤
አንድም ሰው አይቀመጥባትም።
19“አንበሳ ከዮርዳኖስ ደኖች፣
ወደ ግጦሽ ሜዳ ብቅ እንደሚል፣
እኔም በኤዶም ላይ ድንገት እወጣለሁ፤ ከምድሩም አባርረዋለሁ።
የመረጥሁትን በርሱ ላይ እሾማለሁ፤
እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ማንስ ሊገዳደረኝ ይችላል?
የትኛውስ እረኛ ሊቋቋመኝ ይችላል?”
20ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶም ላይ ያቀደውን፣
በቴማን በሚኖሩትም ላይ ያሰበውን ሐሳብ ስሙ፤
ታናናሹ መንጋ ተጐትቶ ይወሰዳል፤
በእነርሱም ምክንያት መሰማሪያቸውን ፈጽሞ ያጠፋል።
21በውድቀታቸው ድምፅ ምድር ትናወጣለች፤
ጩኸታቸውም እስከ ቀይ ባሕር#49፥21 ዕብራይስጡ ያም ሱፍ ይላል፤ ትርጕሙ የሸንበቆ ባሕር ማለት ነው። ያስተጋባል።
22እነሆ፤ እንደ ንስር ተወርውሮ ይወርድባታል፤
ክንፎቹንም በባሶራ ላይ ይዘረጋል፤
በዚያ ቀን የኤዶም ጦረኞች ልብ፣
በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ልብ ይሆናል።
ስለ ደማስቆ የተነገረ መልእክት
23ስለ ደማስቆ፣
“ክፉ ወሬ ሰምተዋልና፣
ሐማትና አርፋድ ደንግጠዋል፤
እንደ#49፥23 ዕብራይስጡ በተናወጠ ይላል። ተናወጠ ባሕርም ታውከዋል፤
ልባቸውም ቀልጧል።
24ደማስቆ ተዳከመች፤
ትሸሽም ዘንድ ወደ ኋላ ተመለሰች፤
ብርክ ያዛት፣
ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣
ጭንቅና መከራ ዋጣት።
25ደስ የምሰኝባት፣
የታወቀችው ከተማ እንዴት ተተወች?
26በርግጥ ወንዶች ወጣቶቿ በየአደባባዩ ይረግፋሉ፤
በዚያ ቀን ወታደሮቿ ሁሉ ይወድቃሉ፤”
ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤
27“በደማስቆ ቅጥር ላይ እሳት እለኵሳለሁ፤
የቤን ሃዳድንም ዐምባ ይበላል።”
ስለ ቄዳርና ስለ ሐጾር የተነገረ መልእክት
28የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ወጋቸው ስለ ቄዳርና ስለ ሐጾር መንግሥታት የተነገረ፤
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ተነሡ፣ ቄዳርን ውጉ፤
የምሥራቅንም ሕዝብ ደምስሱ።
29ድንኳኖቻቸውና መንጎቻቸው ይወሰዳሉ፤
መጠለያቸውና ግመሎቻቸው ሳይቀሩ፣
ከነዕቃዎቻቸው ይነጠቃሉ፤
ሰዎች፣ ‘ሽብር በሽብር ላይ መጥቶባቸዋል፤’
እያሉ ይጮኹባቸዋል።
30“በሐጾር የምትኖሩ ሆይ፣
በጥድፊያ ሽሹ፤ በጥልቅ ጕድጓድ ተሸሸጉ፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በእናንተ ላይ ጠንክሯልና፣
ወረራም ዶልቶባችኋል።
31“ተነሡ፣ ተዘልሎ የተቀመጠውን፣
በራሱ ተማምኖ የሚኖረውን ሕዝብ ውጉ፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
“መዝጊያና መቀርቀሪያ በሌለው፤
ለብቻው በሚኖረው ሕዝብ ላይ ዝመቱ።
32ግመሎቻቸው ይዘረፋሉ፤
ከብቶቻቸውንም አንጋግተው ይነዱባቸዋል፤
ጠጕሩን የሚቀነብበውን ወገን#49፥32 ወይም በሩቅ ስፍራ ያለውን
እበትናለሁ፤ ከየአቅጣጫው መዓት አመጣባችኋለው።”
ይላል እግዚአብሔር።
33“ሐጾር የቀበሮዎች መፈንጫ፣
ለዘላለም ባድማ ትሆናለች፤
ማንም በዚያ አይኖርም፤
የሚቀመጥባትም አይገኝም።”
ስለ ኤላም የተነገረ መልእክት
34በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ፣ ስለ ኤላም ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤
35የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ የኀያልነቷን መሠረት፣
የኤላምን ቀስት እሰብራለሁ።
36ከአራቱ የሰማይ ማእዘናት፣
በኤላም ላይ አራቱን ነፋሳት አመጣለሁ፤
ወደ አራቱም ነፋሳት እበትናቸዋለሁ፤
ከኤላም የሚማረኩት የማይደርሱበት፣
አገር አይገኝም።
37ነፍሳቸውን በሚሹ ጠላቶቻቸው ፊት፣
ኤላምን አርበደብዳለሁ፤
በላያቸው ላይ መዓትን፣
ይኸውም ቍጣዬን አመጣባቸዋለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
“ፈጽሜ አስካጠፋቸውም ድረስ፣
በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።
38ዙፋኔን በኤላም እዘረጋለሁ፤
ነገሥታቷንና መኳንንቷን አጠፋለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር።
39“ነገር ግን የኋላ ኋላ፣
የኤላምን ምርኮ እመልሳለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.