ኤርምያስ 38
38
ኤርምያስ በውሃ ጕድጓድ ውስጥ ተጣለ
1ኤርምያስ ለሕዝቡ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ሰፋጥያስ፣ የጳስኮር ልጅ ጎዶልያስ፣ የሰሌምያ ልጅ ዮካል#38፥1 የዕብራይስጡ ዮካል የሁካል አቻ ስም ነው። እንዲሁም የመልክያ ልጅ ጳስኮር ሰሙ፤ ቃሉም እንዲህ የሚል ነበር፦ 2“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህች ከተማ የሚቀር ሁሉ በሰይፍ፣ በራብ ወይም በቸነፈር ይሞታል፤ ይህን ስፍራ ለቅቆ ወደ ባቢሎናውያን#38፥2 ወይም ከለዳውያን፤ 18፡19 እና 23 ይመ። የሚሄድ ሁሉ ይተርፋል፤ ያመልጣል፤ በሕይወትም ይኖራል።’ 3እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፤ ‘ይህች ከተማ በርግጥ ለባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ዐልፋ ትሰጣለች፤ እርሱም ይይዛታል።’ ”
4መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው በሚናገረው ነገር በዚህች ከተማ የቀሩትን ወታደሮችና ሕዝቡንም ሁሉ ተስፋ የሚያስቈርጥ ስለሆነ መሞት አለበት፤ ይህ ሰው የሕዝቡን መጥፋት እንጂ መልካም ነገር አይሻም።”
5ንጉሡ ሴዴቅያስም፤ “እርሱ በእጃችሁ ነው፤ ንጉሡ እናንተን ተቃውሞ ምንም ማድረግ አይችልም” አለ።
6ስለዚህ ኤርምያስን ወስደው፣ በዘበኞች አደባባይ በነበረው በንጉሡ ልጅ በመልክያ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በገመድም ኤርምያስን ወደ ጕድጓዱ አወረዱት። ጕድጓዱም ጭቃ እንጂ ውሃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ዘልቆ ገባ።
7በቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን የነበረው ኢትዮጵያዊ#38፥7 ከላይኛው አባይ አካባቢ የሚኖር ሊሆን ይችላል፤ ጃንደረባ#38፥7 ወይም ሹም አቤሜሌክ፣ ኤርምያስን በውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ውስጥ እንደ ጣሉት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ሳለ፣ 8አቤሜሌክ ከቤተ መንግሥት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው፤ 9“ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች በነቢዩ በኤርምያስ ላይ ባደረጉት ነገር ሁሉ ክፋትን አድርገዋል፤ ከከተማዪቱም እንጀራ በጠፋ ጊዜ በራብ እንዲሞት ጕድጓድ ውስጥ ጥለውታል።”
10ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፣ “ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ይዘህ ሂድ፤ ነቢዩ ኤርምያስንም ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው” ብሎ አዘዘው።
11አቤሜሌክም ሰዎቹን ይዞ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ሥር ወዳለው ክፍል ሄደ፤ ያረጀ ጨርቅና ያለቀ ልብስ ከዚያ ወስዶ ወደ ኤርምያስ ወደ ጕድጓዱ ውስጥ በገመድ አወረደለት። 12ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን፣ “ይህን ያረጀ ጨርቅና ያረጀ ልብስ ገመዱ እንዳይከረክርህ በብብትህ ሥር አድርገው” አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ፤ 13እነርሱም በገመዱ ጐትተው ከጕድጓዱ አወጡት። ኤርምያስም በዘበኞች አደባባይ ሰነበተ።
ሴዴቅያስ ኤርምያስን እንደ ገና አነጋገረው
14ንጉሡ ሴዴቅያስ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ልኮ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሦስተኛው በር አስመጣውና፤ “አንድ ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ” አለው።
15ኤርምያስም ሴዴቅያስን፣ “መልስ ብሰጥህ አትገድለኝምን? ምክር ብሰጥህ አትሰማኝም” አለው።
16ንጉሥ ሴዴቅያስ፣ “ለኤርምያስ፣ እስትንፋስ የሰጠ ሕያው እግዚአብሔርን! በርግጥ አልገድልህም፤ ሕይወትህንም ለሚሿት አሳልፌ አልሰጥም” ብሎ በምስጢር ማለለት።
17ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለባቢሎን ንጉሥ የጦር መኰንኖች እጅህን ብትሰጥ፣ ሕይወትህ ትተርፋለች፤ ይህችም ከተማ አትቃጠልም፤ አንተና ቤተ ሰብህም በሕይወት ትኖራላችሁ። 18ለባቢሎን ንጉሥ የጦር መኰንኖች እጅህን ባትሰጥ ግን ይህች ከተማ ለባቢሎናውያን ዐልፋ ትሰጣለች፤ እነርሱም ያቃጥሏታል፤ አንተም ራስህ ከእጃቸው አታመልጥም።’ ”
19ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን፣ “ወደ ባቢሎን የኰበለሉት አይሁድ እንዲያላግጡብኝ፣ ባቢሎናውያን ለእነርሱ አሳልፈው ይሰጡኛል ብዬ እፈራለሁ” አለው።
20ኤርምያስም እንዲህ አለው፤ “አሳልፈው አይሰጡህም፤ ብቻ የምነግርህን የእግዚአብሔር ቃል ታዘዝ፤ መልካም ይሆንልሃል፤ ሕይወትህም ትተርፋለች። 21እጅህን ለመስጠት እንቢ ብትል ግን፣ እግዚአብሔር የገለጠልኝ ነገር ይህ ነው፤ 22በይሁዳ ቤተ መንግሥት የቀሩ ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎናውያን ባለ ሥልጣኖች ይወሰዳሉ፤ ሴቶቹም እንዲህ ይላሉ፤
“ ‘እነዚያ የተማመንህባቸው ወዳጆችህ፣
አሳሳቱህ፤ አሸነፉህ።
እግርህ ጭቃ ውስጥ ተሰንቅሯል፤
ወዳጆችህ ጥለውህ ሄደዋል።’
23“ሚስቶችህና ልጆችህ ሁሉ ተወስደው ለባቢሎናውያን ይሰጣሉ፤ አንተም ራስህ በባቢሎን ንጉሥ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።”#38፥23 ወይም ይህችም ከተማ በእሳት እንድትቃጠል ምክንያት ትሆናላችሁ
24ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው፤ “ስለዚህ ስለ ተነጋገርነው ነገር ማንም አይወቅ፤ አለዚያ ትሞታለህ። 25መኳንንቱ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ሰምተው ወደ አንተ ቢመጡና፣ ‘ንጉሡን ምን እንዳልኸው፣ ንጉሡም ምን እንዳለህ ንገረን፤ ሳትደብቅ ንገረን፤ አለዚያ እንገድልሃለን’ ቢሉህ፣ 26‘በዚያ እንዳልሞት ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ ንጉሡን ስለምን ነበር’ በላቸው።”
27መኳንንቱ ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁት፤ እርሱም ንጉሡ ያዘዘውን ቃል ሁሉ ነገራቸው፤ ከንጉሡ ጋር የተነጋገሩትን ነገር የሰማ አንድም ሰው ስላልነበረ፣ ከዚህ በላይ አላነጋገሩትም።
28ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ ኤርምያስ በዘበኞች አደባባይ ተቀመጠ።
Currently Selected:
ኤርምያስ 38: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.