“ ‘ለእስራኤል ቤትና ለይሁዳ ቤት የገባሁትን የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል እግዚአብሔር። “ ‘በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ፣ ከዳዊት ቤት ጻድቅ ቅርንጫፍ አበቅላለሁ፤ በምድሪቱም ፍትሕንና ጽድቅን ያደርጋል። በዚያ ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት ትኖራለች፤ የምትጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል።’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ከዳዊት ዘር በእስራኤል ቤት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አይታጣም፤ ሌዋውያን ከሆኑት ካህናትም የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእህል ቍርባን ለማቃጠልና ሌላውንም መሥዋዕት ለመሠዋት ሁልጊዜ በፊቴ የሚቆም ሰው አይታጣም።’ ” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለቀንና ለሌሊት የወሰንሁትን ሥርዐት በማፋለስ ቀንና ሌሊት በተወሰነላቸው ጊዜ እንዳይፈራረቁ ኪዳኔን ማፍረስ ብትችሉ፣ በዚያ ጊዜ ከአገልጋዬ ከዳዊት ጋራ የገባሁትን ኪዳን፣ እንዲሁም በፊቴ በክህነት ከሚያገለግሉት ሌዋውያን ጋራ የገባሁትን ኪዳን ማፍረስ ይቻላል፤ ዳዊትም ከእንግዲህ በዙፋኑ ላይ የሚነግሥ ዘር አይኖረውም። የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እንዲሁም በፊቴ የሚቆሙትን ሌዋውያን እንደማይቈጠሩ እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደማይሰፈር የባሕር አሸዋ አበዛቸዋለሁ።’ ” የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ይህ ሕዝብ፣ ‘እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁለቱን መንግሥታት ጥሏል’ እንደሚሉ አላስተዋልህምን? ሕዝቤን ንቀዋል፤ እንደ ሕዝብም አልቈጠሯቸውም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የቀንና የሌሊት ኪዳኔን፣ የሰማይንና የምድርንም ሥርዐት ያጸናሁ እኔ ካልሆንሁ፣ የያዕቆብንና የአገልጋዬን የዳዊትን ዘር እጥላለሁ፤ ከልጆቹም በአብርሃም፣ በይሥሐቅና በያዕቆብ ዘር ላይ ገዥ እንዲሆኑ አልመርጥም፤ ይህንም የምለው ምርኳቸውን ስለምመልስና ስለምራራላቸው ነው።’ ”
ኤርምያስ 33 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤርምያስ 33
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤርምያስ 33:14-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች