ኤርምያስ 3
3
1“ሰው ሚስቱን ቢፈታ፣
እርሷም ሄዳ ሌላ ሰው ብታገባ፣
ወደ እርሷ ይመለሳልን?
ምድሪቱስ ፈጽማ አትረክስምን?
አንቺ ግን ከብዙ ወዳጆችሽ ጋር አመንዝረሻል፤
ታዲያ አሁን ወደ እኔ መመለስ ትፈልጊያለሽን?”
ይላል እግዚአብሔር።
2“እስቲ ቀና ብለሽ ጭር ያሉትን ኰረብቶች ተመልከቺ፣
በርኩሰት ያልተጋደምሽበት ቦታ ይገኛልን?
በበረሓ እንደ ተቀመጠ ዘላን ዐረብ፣
በየመንገዱ ዳር ተቀምጠሽ ወዳጆችሽን ጠበቅሽ።
በዝሙትሽና በክፋትሽ፣
ምድሪቱን አረከስሽ።
3ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፤
ኋለኛው ዝናብም ጠፋ።
አንቺ ግን አሁንም የጋለሞታ ገጽታ አለብሽ፤
ዐይንሽን በዕፍረት አልሰብር ብለሻል።
4አሁንም ወደ እኔ ተጣርተሽ፣
‘አባቴ፣ የልጅነት ወዳጄ፣
5ሁልጊዜ ትቈጣለህን?
ቍጣህስ ለዘላለም ነውን?’ አላልሽኝም?
የምትናገሪው እንዲህ ነው፤
ይሁን እንጂ የቻልሽውን ክፋት ሁሉ ታደርጊያለሽ።”
ከዳተኛዋ እስራኤል
6 እግዚአብሔር በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፤ “ከዳተኛዪቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ከፍ ወዳለው ኰረብታ ሁሉ ወጥታ፣ ወደ ለመለመው ዛፍ ሥር ሁሉ ሄዳ በዚያ አመነዘረች። 7ይህን ሁሉ ካደረገች በኋላ፣ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፤ ሆኖም አልተመለሰችም፤ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አየች። 8ለከዳተኛዪቱ እስራኤል ስለ ምንዝርናዋ ሁሉ የፍች ወረቀቷን ሰጥቼ አባረርኋት። ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አይታ እንዳልፈራች አየሁ፤ ወጥታም አመነዘረች። 9በቅሌቷም ምድሪቱን አረከሰች፤ ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች፤ 10ይህም ሁሉ ሆኖ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳ ወደ እኔ የተመለሰችው በማስመሰል እንጂ በሙሉ ልቧ አልነበረም” ይላል እግዚአብሔር።
11 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ከከሓዲዋ ይሁዳ ይልቅ ከዳተኛዪቱ እስራኤል ጻድቅ ሆና ተገኘች። 12ሂድና ይህን መልእክት ወደ ሰሜን እንዲህ ብለህ ተናገር፤
“ ‘ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሽ’ ይላል እግዚአብሔር፤
‘እኔ መሓሪ ስለሆንሁ፣
ከእንግዲህ በቍጣ ዐይን አላይሽም’
ይላል እግዚአብሔር። ‘ለዘላለም አልቈጣም።
13በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅሽ፣
ክብርሽንም ለእንግዶች አማልክት፣
በየለምለሙ ዛፍ ሥር አሳልፈሽ በመስጠት፣
ለእኔ ባለመታዘዝሽ፣
በደለኛ መሆንሽን ይህን አንድ ነገር ብቻ እመኚ’ ”
ይላል እግዚአብሔር።
14“ከዳተኛ ልጆች ሆይ፤ እኔ ባለቤታችሁ ነኝና ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከአንድ ከተማ አንድ፣ ከአንድ ነገድ ሁለት መርጫችሁ ወደ ጽዮን አመጣችኋለሁ። 15እንደ ልቤም የሆኑ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የሚመሯችሁን እረኞች እሰጣችኋለሁ። 16ቍጥራችሁ በምድሪቱ እጅግ በሚበዛበት ጊዜም” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚያ ዘመን፣ ‘የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት’ ብለው ከእንግዲህ አይጠሩም፤ ትዝ አይላቸውም፤ አያስታውሱትምም፤ አይጠፋም፤ ሌላም አይሠራም። 17በዚያ ጊዜ ኢየሩሳሌምን፣ ‘የእግዚአብሔር ዙፋን’ ብለው ይጠሯታል፤ መንግሥታትም ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ለማክበር በኢየሩሳሌም ይሰበሰባሉ፤ የክፉ ልባቸውንም እልኸኝነት ከእንግዲህ አይከተሉም። 18በዚያን ዘመን የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት በአንድነት ሆነው ከሰሜን ምድር ለአባቶቻቸው ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይመጣሉ።
19“እኔም፣
“ ‘የተመረጠችውን ምድር፣
የትኛውም ሕዝብ ያላገኘውን የተዋበች ርስት ልሰጥሽ፣
እንደ ወንዶች ልጆቼ ምንኛ በደስታ ልቍጠርሽ’ አልሁ፤
‘አባቴ’ ብለሽ የምትጠሪኝ፣
እኔንም ከመከተል ዘወር የማትዪ መስሎኝ ነበር።
20የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለባሏ ታማኝ እንዳልሆነች ሚስት፣
ስታታልሉኝ ኖራችኋል፤”
ይላል እግዚአብሔር።
21 እግዚአብሔር አምላካቸውን በመርሳት፣
መንገዳቸውን አጣመዋልና፣
የእስራኤል ሕዝብ ጩኸት፣
አሳዛኝ ልቅሶ ባድማ ከሆኑት ኰረብታዎች ተሰማ።
22“እናንት ከዳተኞች ልጆች ተመለሱ፤
ከዳተኝነታችሁን እፈውሳለሁ።
“አንተ እግዚአብሔር አምላካችን ነህና፤
አዎን፤ ወደ አንተ እንመጣለን።
23በርግጥ በኰረብቶች ላይ፣
እንዲሁም በተራሮች ላይ፣ ሆ! ብለን መውጣታችን መታለል ነው፤
በርግጥ የእስራኤል መዳን፣
በአምላካችን በእግዚአብሔር ነው።
24ከለጋ ዕድሜያችን ጀምሮ፣
የአባቶቻችንን የድካም ፍሬዎች፣
በጎቻቸውንና ከብቶቻቸውን፣
ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን፣ ነውረኛ ጣዖቶች በሏቸው።
25እንግዲህ ዕፍረታችንን ተከናንበን እንተኛ፤
ውርደታችንም ይሸፍነን፤
እኛም አባቶቻችንም፣
እግዚአብሔር አምላካችንን በድለናልና፤
ከልጅነታችን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣
አምላካችንን እግዚአብሔርን አልታዘዝንም።”
Currently Selected:
ኤርምያስ 3: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.