ኤርምያስ 18
18
በሸክላ ሠሪው ቤት
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ 2“ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፤ በዚያ መልእክቴን እሰጥሃለሁ።” 3እኔም ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ወረድሁ፤ ሸክላውንም በመንኰራኵር ላይ ይሠራ ነበር። 4ከጭቃ ይሠራው የነበረውም ሸክላ በእጁ ላይ ተበላሸ፤ ሸክላ ሠሪውም በሚፈልገው ሌላ ቅርጽ መልሶ አበጀው።
5ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 6“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ሸክላ ሠሪው እንደሚሠራው፣ እኔ በእናንተ ላይ መሥራት አይቻለኝምን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ጭቃው በሸክላ ሠሪው እጅ እንዳለ፣ እናንተም እንዲሁ በእጄ ውስጥ ናችሁ። 7አንድ ሕዝብ ወይም መንግሥት እንዲነቀል፣ እንዲፈርስና እንዲጠፋ በተናገርሁ ጊዜ፣ 8ያስጠነቀቅሁት ሕዝብ ከክፋቱ ቢመለስ፣ እኔ ላደርስበት ያሰብሁትን ክፉ ነገር እተዋለሁ። 9በሌላም ጊዜ አንድን ሕዝብ ወይም መንግሥት አንጸውና እተክለው ዘንድ ተናግሬ፣ 10በፊቴ ክፉ ነገር ቢያደርግና ባይታዘዘኝ፣ አደርግለታለሁ ብዬ ያሰብሁትን መልካም ነገር አስቀርበታለሁ።
11“አሁንም እንግዲህ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ጥፋትን እያዘጋጀሁላችሁ ነው፤ ክፋትንም እየጠነሰስሁላችሁ ነው። ስለዚህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ተግባራችሁን አቅኑ።” ’ 12እነርሱ ግን፣ ‘በከንቱ አትድከም፤ ባቀድነው እንገፋበታለን፤ እያንዳንዳችንም የክፉ ልባችንን እልኸኝነት እንከተላለን’ ይላሉ።”
13ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እስኪ አሕዛብን፣
‘እንዲህ ዐይነት ነገር በመካከላችሁ ተሰምቶ ያውቃል?’ ብላችሁ ጠይቁ።
ድንግሊቱ እስራኤል፣
እጅግ ክፉ ነገር አድርጋለች።
14የሊባኖስ ተራራ ድንጋያማ ተረተር፣
በረዶ ተለይቶት ያውቃልን?
ከጋራው የሚወርደውስ ቀዝቃዛ ውሃ፤
መፍሰሱን ያቋርጣልን?#18፥14 በዕብራይስጡ የዚህ ዐረፍተ ነገር ትርጕም በግልጽ አይታወቅም።
15ሕዝቤ ግን ረስቶኛል፤
ለማይረቡ ነገሮች ዐጥኗል፣
በራሱ መንገድ፣
በቀደሞው ጐዳና ተሰናክሏል፤
በሻካራው መሄጃ፣
ባልቀናውም ጥርጊያ መንገድ ሄዷል።
16ምድራቸው ባድማ፣
ለዘላለም መሣለቂያ ይሆናል፤
በዚያ የሚያልፍ ሁሉ ይደነቃል፤
በመገረምም ራሱን ይነቀንቃል።
17ከምሥራቅ እንደሚወጣ ነፋስ፣
በጠላቶቻቸው ፊት እበትናቸዋለሁ፤
በመጥፊያቸው ቀን፣
ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም።”
18እነርሱም፣ “ሕግ ከካህናት፣ ምክር ከጠቢባን፣ ቃልም ከነቢያት ስለማይታጣ ኑና በኤርምያስ ላይ እንማከር፤ ኑ፤ በአንደበታችን እናጥቃው፣ እርሱ የሚናገረውንም ሁሉ አንስማ” አሉ።
19 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስማኝ፤
ባላንጣዎቼ የሚሉትን አድምጥ።
20የመልካም ተግባር ወሮታው ክፉ ነውን?
እነርሱ ግን ጕድጓድ ቈፈሩልኝ፤
ቍጣህን ከእነርሱ እንድትመልስ፣
በፊትህ ቆሜ፣
ስለ እነርሱ እንደ ተናገርሁ ዐስብ።
21ስለዚህ ልጆቻቸውን ለራብ፣
ለሰይፍም ስለት አሳልፈህ ስጥ፤
ሚስቶቻቸው የወላድ መካን፣ መበለትም ይሁኑ፤
ወንዶቻቸው በሞት ይቀሠፉ፤
ጕልማሶቻቸው በጦር ሜዳ ለሰይፍ ይዳረጉ።
22ሊይዙኝ ጕድጓድ ስለ ቈፈሩ፣
ለእግሮቼም በስውር ወጥመድ ስለ ዘረጉ፣
በድንገት ወራሪ ስታመጣባቸው፣
ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ።
23አንተ ግን እግዚአብሔር ሆይ፤
ሊገድሉኝ ያሤሩብኝን ሤራ ሁሉ ታውቃለህ፤
በደላቸውን ይቅር አትበል፤
ኀጢአታቸውንም ከፊትህ አትደምስስ፤
በፊትህ ወድቀው የተጣሉ ይሁኑ፤
በቍጣህም ጊዜ አትማራቸው።
Currently Selected:
ኤርምያስ 18: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.