የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኤርምያስ 17

17
1“የይሁዳ ኀጢአት በብረት ብርዕ፣
በሾለ የአልማዝ ጫፍ፣ ተጽፏል፤
በልባቸው ጽላት፣
በመሠዊያቸውም ቀንዶች ላይ ተቀርጿል።
2ልጆቻቸው እንኳ ሳይቀሩ፣
በለመለሙ ዛፎች ሥር፣
ከፍ ባሉ ኰረብቶችም ላይ ያሉትን፣
መሠዊያቸውንና አሼራ የተባለችውን ጣዖት ምስል#17፥2 ወይም የአሼራ ዐጸድ ያስባሉ።
3በአገርህ ሁሉ ከተፈጸመው ኀጢአት የተነሣ፣
በምድሪቱ ያለህ ተራራዬ፣#17፥3 ወይም በምድሪቱ ያሉ ተራራዎችን
ሀብትህንና ንብረትህን ሁሉ፣
መስገጃ ኰረብቶችህንም ጭምር፣
ለብዝበዛ አደርገዋለሁ።
4በገዛ ጥፋትህ፣
የሰጠሁህን ርስት ታጣለህ፤
በማታውቀውም ምድር፣
ለጠላቶችህ ባሪያ አደርግሃለሁ፤
ለዘላለም የሚነድደውን፣
የቍጣዬን እሳት ጭረሃልና።”
5 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በሰው የሚታመን፣
በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣
ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።
6በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፤
መልካም ነገር ሲመጣ አያይም፤
ሰው በሌለበት በጨው ምድር፣
በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል።
7“ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣
መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
8በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣
ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣
ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤
ቅጠሉም ዘወትር እንደ ለመለመ ነው፤
በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤
ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”
9የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤
ፈውስም የለውም፤
ማንስ ሊረዳው ይችላል?
10“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣
እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣
ልብን እመረምራለሁ፤
የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”
11ሀብትን በግፍ የሚያከማች ሰው፣
ያልፈለፈለችውን ጫጩት እንደምትታቀፍ ቆቅ ነው፤
በዕድሜው አጋማሽ ትቶት ይሄዳል፤
በመጨረሻም ሞኝነቱ ይረጋገጣል።
12የመቅደሳችን ስፍራ፣
ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።
13የእስራኤል ተስፋ እግዚአብሔር ሆይ፤
ጥለውህ የሚሄዱ ሁሉ ያፍራሉ፤
ፊታቸውን ከአንተ የሚመልሱ በምድር ውስጥ ይጻፋሉ፤
የሕይወትን ውሃ ምንጭ፣
እግዚአብሔርን ትተዋልና።
14 እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈውሰኝ፤ እፈወሳለሁ፤
አድነኝ እኔም እድናለሁ፤
አንተ ምስጋናዬ ነህና።
15እነርሱ ደጋግመው፣
የእግዚአብሔር ቃል የት አለ?
እስቲ አሁን ይፈጸም!” ይሉኛል።
16እረኛ ሆኜ አንተን ከማገልገል ወደ ኋላ አላልሁም፤
ክፉ ቀን እንዳልተመኘሁ ታውቃለህ፤
ከአንደበቴ የሚወጣውም በፊትህ ግልጽ ነው።
17አስደንጋጭ አትሁንብኝ፤
በመከራ ቀን መሸሸጊያዬ አንተ ነህ።
18አሳዳጆቼ ይፈሩ፤
እኔን ግን ከዕፍረት ጠብቀኝ፤
እነርሱ ይደንግጡ፤
እኔን ግን ከድንጋጤ ሰውረኝ፤
ክፉ ቀን አምጣባቸው፤
በዕጥፍ ድርብ ጥፋት አጥፋቸው።
ሰንበትን ማክበር
19 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ሄደህ የይሁዳ ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ በር በሌሎቹም የኢየሩሳሌም በሮች ሁሉ ቁም፤ 20እንዲህም በላቸው፤ ‘በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ነገሥታት ሆይ፤ የይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳታስገቡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 22አባቶቻችሁን እንዳዘዝኋቸው ሰንበትን አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ከየቤታችሁ ሸክም ይዛችሁ አትውጡ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ።” 23እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም ዐንገታቸውን አደነደኑ። 24ነገር ግን በጥንቃቄ ብትታዘዙኝ ይላል እግዚአብሔር፤ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ይዛችሁ ባትገቡ፣ የሰንበትንም ቀን ምንም ሳትሠሩ ብትቀድሱት፣ 25በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መኳንንታቸው በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ በፈረሶችና በሠረገሎች ተቀምጠው በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ታጅበው ይመጣሉ፤ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች። 26ሰዎች ከይሁዳ ከተሞች፣ ከኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ ከብንያምም አገር፣ ከቈላውና ከደጋው አገር እንዲሁም ከኔጌቭ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ ዕጣንና የምስጋና መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ። 27ነገር ግን የሰንበትን ቀን ሳትቀድሱ፣ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች በመግባት ትእዛዜን ብትጥሱ፣ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ምሽጎቿን የሚበላ፣ የማይጠፋ እሳት እጭራለሁ።’ ”

Currently Selected:

ኤርምያስ 17: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ