ኤርምያስ 13
13
ከተልባ እግር የተሠራ መቀነት
1 እግዚአብሔር፣ “ሄደህ ከተልባ እግር የተሠራ መቀነት ግዛ፤ ወገብህንም ታጠቅበት፤ ነገር ግን ውሃ አታስነካው” አለኝ። 2ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ መቀነቱን ገዛሁ፤ ወገቤንም ታጠቅሁበት።
3ለሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 4“ገዝተህ የታጠቅህበትን መቀነት ይዘህ ወደ ኤፍራጥስ#13፥4 ወይም ፌሬጥ ሂድ፤ በዚያም በዐለት ንቃቃት ውስጥ ሸሽገው።” 5ስለዚህ እግዚአብሔር በነገረኝ መሠረት ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ ሸሸግሁት።
6ከብዙ ቀን በኋላም እግዚአብሔር፣ “ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያ እንድትሸሽገው የነገርሁህን መቀነት አምጣ” አለኝ። 7እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ፣ መታጠቂያውን ከሸሸግሁበት ቦታ ቈፍሬ አወጣሁ፤ መታጠቂያውም ተበላሽቶ፣ ከጥቅም ውጭም ሆኖ ነበር።
8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የይሁዳን ትዕቢትና የኢየሩሳሌምን እብሪት እንደዚሁ አጠፋለሁ። 10ቃሌን መስማት እንቢ ብለው በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ ሊያመልኳቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን ጣዖቶች የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝቦች ከጥቅም ውጭ እንደ ሆነው እንደዚህ መቀነት ይበላሻሉ። 11መቀነት በሰው ወገብ ላይ እንደሚታሰር፣ መላው የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከእኔ ጋር ተጣብቆ ለስሜ ምስጋናና ክብር፣ የእኔ ሕዝብ እንዲሆንልኝ አድርጌው ነበር፤ ሕዝቤ ግን አልሰማም’ ይላል እግዚአብሔር።
የወይን ጠጅ ማድጋ
12“እንዲህ በላቸው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ ይሞላል’፤ እነርሱም፣ ‘ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ እንደሚሞላ እኛ አናውቅምን?’ ቢሉህ፣ 13እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትን፣ ካህናትን፣ ነቢያትን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሁሉ ጨምሮ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። 14አንዱን ሰው ከሌላው ጋር፣ አባትንና ወንድ ልጅን እርስ በእርስ አጋጫለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር፤ ያለ ሐዘኔታ፣ ያለ ምሕረትና ያለ ርኅራኄ አጠፋቸዋለሁ።’ ”
የትዕቢት ውጤት
15 እግዚአብሔር ተናግሯልና፣
ስሙ፤ ልብ በሉ፤
ትዕቢተኛም አትሁኑ።
16ጨለማን ሳያመጣ፣
በሚጨልሙትም ተራሮች ላይ፣
እግሮቻችሁ ሳይሰናከሉ፣
ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ።
ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ፤
እርሱ ወደ ጨለማ ይለውጠዋል፤
ድቅድቅ ጨለማም ያደርገዋል።
17ባትሰሙ ግን፣
ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ፣
በስውር ታለቅሳለች፤
የእግዚአብሔር መንጋ ተማርኳልና፣
ዐይኔ አምርሮ ያለቅሳል፤
እንባዬም እንደ ጐርፍ ይወርዳል።
18ለንጉሡና ለእናቱ ለእቴጌዪቱ፣
“የክብር ዘውዳችሁ ከራሳችሁ ይወድቃልና፣
ከዙፋናችሁ ውረዱ” በላቸው።
19በኔጌቭ ያሉ ከተሞች ይዘጋሉ፤
የሚከፍታቸውም አይኖርም።
ይሁዳ ሁሉ ተማርኮ ይሄዳል፤
ሙሉ በሙሉም ይዘጋል።
20ዐይኖቻችሁን ከፍታችሁ፣
ከሰሜን የሚመጡትን እዩ።
ለአንቺ የተሰጠው መንጋ፣
የተመካሽባቸው በጎች የት አሉ?
21ልዩ ወዳጆች እንዲሆኑሽ ያስተማርሻቸው፣
ባለ ሥልጣን ሲሆኑብሽ ምን ትያለሽ?
እንደምትወልድ ሴት፣
ምጥ አይዝሽምን?
22“ይህ ለምን ደረሰብኝ?” ብለሽ
ራስሽን ብትጠይቂ፣
ልብስሽን ተገልበሽ የተገፈተርሽው፣
በሰውም እጅ የተንገላታሽው፣
ከኀጢአትሽ ብዛት የተነሣ ነው።
23ኢትዮጵያዊ#13፥23 ዕብራይስጡ ኩሻዊ ይላል (ምናልባት በላይኛው አባይ አካባቢ የሚኖር ሰው ሊሆን ይችላል)። መልኩን፣
ነብርስ ዝንጕርጕርነቱን መለወጥ ይችላልን?
እናንት ክፉ ማድረግ የለመዳችሁትም፣
መልካም ማድረግ አትችሉም።
24“የበረሓ ነፋስ ብትንትኑን እንደሚያወጣው ገለባ፣
እንዲሁ እበታትናችኋለሁ።
25እኔን ረስተሽ፣
በከንቱ አማልክት ስለ ታመንሽ፣
ያወጅሁልሽ ድርሻሽ፣
ዕጣ ፈንታሽ ይህ ነው፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
26“ኀፍረትሽ እንዲገለጥ፣
ልብስሽን ፊትሽ ድረስ እገልባለሁ፤
27በኰረብቶችና በሜዳዎች ላይ፣
አስጸያፊ ተግባርሽን፣
ምንዝርናሽንና ማሽካካትሽን፣
ኀፍረተ ቢስ ግልሙትናሽን አይቻለሁ።
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ወዮልሽ፤
ከርኩሰትሽ የማትጸጂው እስከ መቼ ነው?”
Currently Selected:
ኤርምያስ 13: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.