የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኤርምያስ 11

11
ያልተከበረው ኪዳን
1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ 2“የዚህን ኪዳን ቃል ስማ፤ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሰዎች ንገራቸው፤ 3የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው፤ ‘ለዚህ ኪዳን ቃል የማይታዘዝ ሰው የተረገመ ይሁን፤ 4ይህም ትእዛዝ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር፣ ከብረት ማቅለጫው ምድጃ ባወጣኋቸው ጊዜ ድምፄን ቢሰሙ፣ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቁ፣ እነርሱ ሕዝቤ፣ እኔም አምላካቸው እንድሆን የሰጠኋቸው ቃል ነው፤ 5ዛሬም እንደ ሆነው ሁሉ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለአባቶቻችሁ ለመስጠት የገባሁትን መሐላ እፈጽማለሁ።’ ”
እኔም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሜን” ብዬ መለስሁ።
6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባዮች ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘የዚህን ኪዳን ቃል ስሙ፤ አድርጉትም። 7የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ “ታዘዙኝ” በማለት ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው። 8እነርሱ ግን የክፉ ልባቸውን እልኸኝነት ተከተሉ እንጂ አልታዘዙኝም፤ ጆሯቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም፤ ስለዚህ እንዲከተሉት አዝዤአቸው ያላደረጉትን የዚህን ኪዳን ርግማን ሁሉ አመጣሁባቸው።’ ”
9 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “በይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ዘንድ ዐድማ ተገኝቷል። 10ቃሌን መስማት ወዳልፈለጉት ወደ ቀድሞ አባቶቻቸው ኀጢአት ተመለሱ፤ ሊያገለግሏቸውም ሌሎችን አማልክት ተከተሉ። የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ኪዳን አፈረሱ። 11ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሊያመልጡት የማይችሉትን ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፤ ወደ እኔ ቢጮኹም አልሰማቸውም። 12የይሁዳ ከተሞችና የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ሄደው ይጮኻሉ፤ እነርሱ ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ ሊረዷቸው አይችሉም። 13ይሁዳ ሆይ፤ የአማልክትህ ቍጥር የከተሞችህን ብዛት ያህል ነው፤ አሳፋሪ ለሆነው ጣዖት፣ ለበኣል ማጠኛ የሠራችኋቸው መሠዊያዎቻችሁ ብዛት የኢየሩሳሌምን መንገዶች ያህል ነው።’
14“በተጨነቁ ጊዜ ወደ እኔ ሲጮኹ አልሰማቸውምና አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን።
15“ወዳጄ፣ ከብዙዎች ጋር ተንኰሏን እየሸረበች፣
በቤቴ ውስጥ ምን ጕዳይ አላት?
ስእለት ወይም የመሥዋዕት ሥጋ ቅጣትሽን ሊያስቀርልሽ ይችላልን?
እነዚህንስ በመፈጸም፣ ደስተኛ መሆን
ትችያለሽን?”#11፥15 ወይም ስእለት ወይም የመሥዋዕት ሥጋ ቅጣትሽን ያስቀርልሽ ይችል ይሆን? የዚያን ጊዜ ትደሰቻለሽ
16 እግዚአብሔር፣ የተዋበ ፍሬ ያላት፣
የለመለመች የወይራ ዛፍ ብሎሽ ነበር፤
አሁን ግን በታላቅ ዐውሎ ነፋስ ድምፅ፣
እሳት ያነድድባታል፤
ቅርንጫፎቿ ይሰባበራሉ።
17የእስራኤልና የያዕቆብ ቤት ለበኣል በማጠን ባደረጉት ክፋት ስላስቈጡኝ፣ አንቺን የተከለሽ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክፉ ነገር ዐውጆብሻል።
በኤርምያስ ላይ የተደረገ ሤራ
18 እግዚአብሔር ስውር ዕቅዳቸውን ገለጠልኝ፤ እኔም ዐወቅሁ፤ በዚያን ጊዜ ሥራቸውን አሳይቶኝ ነበርና። 19እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት ነበርሁ፤ እነርሱም፣
“ዛፉን ከፍሬው ጋር እንቍረጥ፤
ከሕያዋን ምድር እናጥፋው፤
ከእንግዲህም ወዲያ ስሙ አይታሰብ”
ብለው እንዳደሙብኝ ዐላወቅሁም ነበር።
20ልብንና ኵላሊትን የምትመረምር፣
በጽድቅም የምትፈርድ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤
ጕዳዬን ላንተ ትቻለሁና፤
በእነርሱ ላይ የምትፈጽመውን በቀል ልይ።
21“እንግዲህ ሕይወትህን ለማጥፋት ለሚሹና፣ ‘በእግዚአብሔር ስም ትንቢት አትናገር፤ አለዚያ በእጃችን ትሞታለህ’ ለሚሉህ ለዓናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ 22ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ እኔ እቀጣቸዋለሁ፤ ጕልማሶቻቸው በሰይፍ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ። 23በሚቀጡበት ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ መዓት ስለማመጣ፣ ከእነርሱ የሚተርፍ አንድም አይኖርም።’ ”

Currently Selected:

ኤርምያስ 11: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ