የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 9

9
አቤሜሌክ
1የይሩባኣል ልጅ አቤሜሌክ ወደ እናቱ ወንድሞች ወደ ሴኬም ሄደ። እነርሱንና የእናቱን ጐሣዎች በሙሉ እንዲህ አላቸው፤ 2“የሴኬምን ነዋሪዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፤ ‘ሰባዎቹ የይሩባኣል ልጆች ቢገዟችሁ ይሻላል ወይስ አንድ ሰው ብቻ?’ የሥጋችሁ ቍራጭ፣ የዐጥንታችሁ ፍላጭ መሆኔን ልብ በሉ።”
3የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ነዋሪዎች በሙሉ ነገሩ፤ አቤሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ዳዳ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል” ብለዋልና። 4እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል#9፥4 0.8 ኪሎ ግራም ያህል ነው ናስ ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት። 5ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩበኣልን ልጆች፣ ወንድሞቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩበኣል የመጨራሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ። 6የሴኬምና የቤት ሚሎ ነዋሪዎች በሙሉ አቤሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ።
7ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ “የሴኬም ነዋሪዎች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ። 8ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
9“የወይራ ዛፍም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?’ አለ።
10“ቀጥሎም ዛፎቹ በለስን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
11“በለስ ግን፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እጅግ ጣፋጭና መልካም የሆነውን ፍሬዬን መስጠት ልተውን?’ አለ።
12“ከዚያም ዛፎቹ የወይን ተክልን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
13“የወይን ተክሉም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ አማልክትንና ሰዎችን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን መስጠት ልተውን?’ አለ።
14“በመጨረሻም ዛፎቹ በሙሉ የእሾኽ ቍጥቋጦን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
15“የእሾኽ ቍጥቋጦውም ዛፎቹን፣ ‘በርግጥ ቀብታችሁ በላያችሁ የምታነግሡኝ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ግን እሳት ከእሾኽ ቍጥቋጦው ይነሣ፤ የሊባኖስንም ዝግባዎች ይብላ!’ አላቸው።
16“እንግዲህ አቤሜሌክን ስታነግሡት በቅንነትና በእውነት አድርጋችሁት ከሆነ፣ ይሩበኣልንና ቤተ ሰቡን በበጎ ዐይን ተመልክታችሁ ላደረገው የሚገባውን አይታችሁለት ከሆነ፣ 17አባቴ ለእናንተ መዋጋቱን፣ ከምድያማውያን እጅ ሊያድናችሁ ሕይወቱን መስጠቱን ዐሰባችሁ ማለት ነው። 18ነገር ግን እናንተ ዛሬ በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ዐመፃችሁ፤ ሰባ ልጆቹን በአንዲት ድንጋይ ላይ ዐረዳችሁ፤ ዘመዳችሁ ስለ ሆነም አባቴ ከባሪያው የወለደውን ልጅ አቤሜሌክን በሴኬም ነዋሪዎች ላይ አነገሣችሁት። 19እንግዲህ ዛሬ በይሩበኣልና በቤተ ሰቡ ላይ ያደረጋችሁት በእውነትና በቅንነት ከሆነ እናንተ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም በእናንተ ደስ ይበለው! 20ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቤሜሌክ ትውጣና እናንተን፣ የሴኬምንና የቤት ሚሎን ነዋሪዎች ትብላ፤ እንዲሁም እሳት ከእናንተ፣ ከሴኬምና ከቤትሚሎን ነዋሪዎች ትውጣና አቤሜሌክን ትብላ።”
21ከዚህ በኋላ ኢዮአታም ሸሽቶ አመለጠ፤ ብኤር ወደ ተባለች ቦታም መጣ፤ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ስለ ነበር እዚያው ይኖር ጀመር።
22አቤሜሌክ እስራኤልን ሦስት ዓመት ከገዛ በኋላ፣ 23እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ነዋሪዎች መካከል ክፉ መንፈስ ሰደደ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች አቤሜሌክን ከዱት። 24እግዚአብሔር ይህን ያደረገውም፣ በሰባው የይሩበኣል ልጆች ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍና ስለ ፈሰሰው ደማቸው፣ ወንድማቸውን አቤሜሌክና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬም ሰዎች ለመበቀል ነው። 25የሴኬም ነዋሪዎችም አቤሜሌክን ሸምቀው የሚጠባበቁትን ሰዎች መደቡ፤ ሰዎቹም እርሱን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በዚያ የሚያልፈውን ሁሉ ዘረፉ፤ ወሬውም ለአቤሜሌክ ደረሰው።
26በዚህ ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ሰዎች ተማመኑበት። 27ወደ ዕርሻ ወጥተው ወይናቸውን ለቅመው ከጨመቁ በኋላ በአምላካቸው ቤት የደስታ በዓል አደረጉ፤ በዚያም እየበሉና እየጠጡ አቤሜሌክን ሰደቡ። 28የአቤድ ልጅ ገዓል እንዲህ አለ፤ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ሴኬምስ ምንድን ናት? እርሱ የይሩበኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የእርሱ ረዳት ሹም አይደለምን? ለሴኬም አባት ለኤሞር ሰዎች ተገዙ፤ ለምን ለአቤሜሌክ እንገዛለን? 29ምነው ይህን ሕዝብ የማዝዘው እኔ በሆንሁ ኖሮ! አቤሜሌክን አስወግደው ነበር፤ ‘ሰራዊትህን አብዝተህ ውጣ#9፥29 ዕብራይስጡ አቤሜሌክን እንዲህ አለው፤ ሰራዊትህን ሁሉ ጥራ! ይላል።!’ እለው ነበር።”
30የከተማዪቱ ገዥ ዜቡል፣ የአቤድ ልጅ ገዓል ያለውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ 31ወደ አቤሜልክም መልእክተኞች በምስጢር ልኮ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሴኬም መጥተው ከተማዪቱ እንድትሸፍትብህ አድርገዋል። 32ስለዚህ በሌሊት ሰዎችህን ይዘህ ወጥተህ ሜዳው ላይ ማድፈጥ አለብህ፤ 33ጧት ፀሓይ ስትወጣም ወደ ከተማዪቱ ገሥግሥ፤ ገዓልና ሰዎቹ ሊገጥሙህ በሚወጡበት ጊዜ እጅህ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርግ።”
34ስለዚህ አቤሜሌክና ሰዎቹ በሙሉ በሌሊት ወጡ፤ በአራት ምድብ ሆነውም በሴኬም አጠገብ አደፈጡ። 35የአቤድ ልጅ ገዓል ከከተማዪቱ ወጥቶ በመግቢያው በር ላይ ሲቆም፣ አቤሜሌክና ሰዎቹ ካደፈጡበት ወጡ።
36ገዓል ባያቸው ጊዜ ዜቡልን፣ “ተመልከት፤ ከተራራው ጫፍ ሕዝብ እየወረደ ነው” አለው።
ዜቡልም መልሶ፣ “የተራሮች ጥላ ሰዎች መስሎ ተሳስተህ” ነው አለው።
37ገዓልም፣ “ተመልከት እንጂ ሕዝብ እኮ ከተራራው ወገብ ላይ እየደረሰ ነው፤ አንዱ ክፍልም በቃላተኞች ዛፍ በኩል አድርጎ እየመጣ ነው” ብሎ እንደ ገና ተናገረ።
38ከዚያም ዜቡል፣ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜልክ ማን ነው? ብለህ የደነፋኸው አሁን የት አለ? ያቃለልሀቸውስ ሰዎች እነዚህ አይደሉምን? በል ውጣና ግጠማቸው” አለው። 39ገዓል የሴኬምን ሰዎች መርቶ በመውጣት አቤሜሌክን ተዋጋው፤ 40ሆኖም አቤሜሌክ አሳደደው፤ እስከ መግቢያው በር ድረስ ባለው መንገድ ሲሸሹም ብዙ ሰዎች ቈስለው ወደቁ። 41አቤሜሌክ በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው።
42በማግስቱም የሴኬም ሕዝብ ወደ ዕርሻ ወጡ፤ ይህም ለአቤሜሌክ ተነገረው፤ 43እርሱም ሰዎቹን አስከትሎ ወጣ፤ ከዚያም ሰዎቹን ሦስት ቦታ መድቦ በዕርሻዎቹ ውስጥ አድፍጠው እንዲጠባበቁ አደረገ። አቤሜሌክ የሴኬም ሰዎች ከከተማዪቱ መውጣታቸውን እንዳየም ካደፈጠበት ሊወጋቸው ተነሣ። 44ከዚያም አቤሜሌክና አብረውት የነበሩ ምድቦች ቦታ ለመያዝ በፍጥነት ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በሚሮጡበት ጊዜ፣ ሌሎቹ ሁለት ምድቦች ደግሞ እየሮጡ ሄደው በዕርሻው ያሉትን ሁሉ ፈጇቸው። 45በዚያን ዕለት አቤሜሌክ ቀኑን ሙሉ ከተማዪቱን ሲወጋ ውሎ በመጨረሻ ያዛት፤ ሕዝቧን ፈጀ፤ ከተማዪቱንም አጠፋ፤ በላይዋም ጨው ዘራባት።
46በሴኬም ግንብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ይህን እንደ ሰሙ፤ በኤልበሪት ቤተ መቅደስ ወዳለው ምሽግ ውስጥ ገቡ። 47አቤሜሌክም በዚያ መመሸጋቸውን ሲሰማ፣ 48እርሱና ሰዎቹ ሁሉ ወደ ሰልሞን ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም መጥረቢያ ወስዶ ጥቂት የዛፍ ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ በትከሻውም ላይ አደረገ። የተከተሉትንም ሰዎች፣ “ፍጠኑ፤ እኔ ሳደርግ ያያችሁትን አድርጉ” ሲል አዘዛቸው። 49ሰዎቹም ሁሉ ቅርንጫፎች ቈርጠው አቤሜሌክን ተከተሉት፤ ቅርንጫፎቹንም ምሽጉ ላይ አስደግፈው በመከመር ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ በእሳት አቃጠሏቸው። ስለዚህ በሴኬም ምሽግ ውስጥ የነበሩት አንድ ሺሕ ያህል ወንዶችና ሴቶች ሞቱ።
50ከዚያም አቤሜሌክ ወደ ቴመስ በመሄድ ከተማዪቱን ከብቦ ያዛት። 51ሆኖም በከተማዪቱ ውስጥ ብርቱ ግንብ ስለ ነበር፣ የከተማዪቱ ሕዝብ በሙሉ ወንድ ሴት ሳይባል ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በውስጥ ዘግተው ወደ ግንቡ ጣሪያ ወጡ። 52አቤሜሌክም ተዋግቶ ግንቡን ያዘ፤ ይሁን እንጂ እሳት ለመለኰስ ወደ ግንቡ መግቢያ አጠገብ እንደ ደረሰ፣ 53አንዲት ሴት ከላይ የወፍጮ መጅ በራሱ ላይ ለቀቀችበት፤ ጭንቅላቱንም አፈረሰችው።
54ወዲያውም ጋሻ ጃግሬውን ጠርቶ፣ “ ‘ሴት ገደለችው’ እንዳይሉ እባክህ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ” አለው። ስለዚህ አገልጋዩ ወጋው፤ እርሱም ሞተ። 55እስራኤላውያንም አቤሜሌክ መሞቱን ሲያዩ ወደ የቤታቸው ተመለሱ።
56አቤሜሌክ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል፣ በአባቱ ላይ ስላደረሰው በደል እግዚአብሔር የእጁን ከፈለው። 57በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር የሴኬምን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰው፤ የይሩበኣል ልጅ የኢዮአታም ርግማን ደረሰባቸው።

Currently Selected:

መሳፍንት 9: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ