የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መሳፍንት 16:23-31

መሳፍንት 16:23-31 NASV

በዚህ ጊዜ የፍልስጥኤማውያን ገዦች፣ “አምላካችን ዳጎን፣ ጠላታችን ሳምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል” ብለው በመደሰት ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ለማቅረብ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሳምሶንን ባዩት ጊዜ፣ አምላካቸውን ዳጎንን በማመስገን፣ “ምድራችንን ያጠፋውን፣ ብዙ ሰው የገደለብንን፣ ጠላታችንን፣ አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” አሉ። እጅግ ደስ ባላቸው ጊዜ፣ “እንዲያዝናናን ሳምሶንን አምጡት” አሉ፤ ስለዚህ ሳምሶንን ከእስር ቤት ጠርተው አስመጡት፤ በፊታቸውም ተጫወተ። በምሰሶዎቹ መካከል ባቆሙት ጊዜ፣ ሳምሶን እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ፣ “ቤተ ጣዖቱን ደግፈው ወደ ያዙት ምሰሶዎች አስጠጋኝና ልደገፋቸው” አለው። በዚህ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ቤተ ጣዖቱን ሞልተውት ነበር፤ የፍልስጥኤማውያን ገዦችም በሙሉ በዚያ ነበሩ፤ ሳምሶን ሲጫወት ለማየት ሦስት ሺሕ ያህል ወንዶችና ሴቶች በጣራው ላይ ነበሩ። ሳምሶንም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ። አምላክ ሆይ፤ እባክህን አንድ ጊዜ ብቻ ብርታት ስጠኝና ስለ ጠፉት ዐይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አንዴ ልበቀላቸው።” ከዚያም ቤተ ጣዖቱን መካከል ላይ ደግፈው የያዙትን ሁለት ምሰሶዎች አንዱን በቀኙ፣ አንዱን በግራ እጁ ዐቅፎ በመያዝ፣ “ከፍልስጥኤማውያን ጋር አብሬ ልሙት” በማለት ባለ ኀይሉ ሲገፋው፣ ቤተ ጣዖቱ በገዦቹና በውስጡ በነበሩት በሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ላይ ወደቀባቸው። ስለዚህ በሕይወት ከኖረበት ጊዜ ይልቅ በሞቱ ጊዜ ብዙ ሰው ገደለ። ወንድሞቹና መላው የአባቱ ቤተ ሰብ ሬሳውን ለማምጣት ወደዚያ ወረዱ፤ አምጥተውም የአባቱ የማኑሄ መቃብር ባለበት በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ቀበሩት። ሳምሶን በእስራኤል ላይ ሃያ ዓመት ፈራጅ ሆነ።