ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ለማየት ሄደ፤ እርሱም፣ “ሚስቴ ወዳለችበት ጫጕላው ቤት ልግባ” አለ፤ አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም። አባትየውም፣ “ፈጽሞ የጠላሃት መሆንህን ስለ ተረዳሁ ለሚዜህ ድሬለታለሁ፤ ታናሽ እኅቷ ከርሷ ይልቅ ውብ አይደለችምን? እርሷን አግባት” አለው። ሳምሶንም መልሶ፣ “ከእንግዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ በሚደርሰው ጕዳት ተጠያቂ አልሆንም” አላቸው። ከዚያም ወጥቶ በመሄድ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ የሁለት ሁለቱን ጭራ አንድ ላይ ካሰረ በኋላ ችቦ ወስዶ ጥንድ ሆኖ ከተያያዘው ጭራ ጋራ አሰረው። ችቦውን በእሳት አቀጣጥሎ ቀበሮቹን በፍልስጥኤማውያን የእህል አዝመራ ላይ ለቀቃቸው፤ ነዶውንና የቆመውን አዝመራ እንዲሁም የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠለ። ፍልስጥኤማውያን፣ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ፣ “ሚስቱ ለሚዜው ስለ ተሰጠችበት የተምናዊው ዐማች ሳምሶን ነው” የሚል መልስ አገኙ። ስለዚህም ፍልስጥኤማውያን ወጥተው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጥለው ገደሏቸው። ሳምሶንም፣ “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ ሳልበቀላችሁ አልመለስም” አለ። ክፉኛ መታቸው፤ ከእነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኤጣም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ። ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ። የይሁዳም ሰዎች፣ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ልናስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው። ከዚያም ሦስት ሺሕ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤጣም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፣ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ሳምሶንም፣ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው። እነርሱም፣ “አስረን ለፍልስጥኤማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት። ሳምሶንም፣ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።
መሳፍንት 15 ያንብቡ
ያዳምጡ መሳፍንት 15
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መሳፍንት 15:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች