እንግዲህ እናንተ ሀብታሞች ስሙ፤ ስለሚደርስባችሁ መከራ አልቅሱ፤ ዋይ ዋይም በሉ። ሀብታችሁ ሻግቷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል። ወርቃችሁና ብራችሁ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሰክራል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላዋል፤ ለመጨረሻው ዘመን ሀብትን አከማችታችኋል። ልብ በሉ፤ ዕርሻችሁን ሲያጭዱ ለዋሉ ሠራተኞች ያልከፈላችሁት ደመወዝ በእናንተ ላይ ይጮኻል፤ የዐጫጆቹም ጩኸት ሁሉን ቻይ ወደ ሆነው ጌታ ጆሮ ደርሷል። በምድርም ላይ በምቾትና በመቀማጠል ኖራችኋል፤ ለዕርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል። እናንተን ያልተቃወሙትን ንጹሓን ሰዎች ኰንናችኋል፤ ገድላችኋልም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቧል። ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አታጕረምርሙ፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል፤ እነሆ፤ ፈራጁ በበር ላይ ቆሟል። ወንድሞች ሆይ፤ በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያት የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ ሆይ፤ በሰማይ ወይም በምድር ወይም በማናቸውም ነገር ቢሆን አትማሉ፤ “አዎ” ቢሆን አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ቢሆን አይደለም ይሁን፤ አለዚያ ይፈረድባችኋል።
ያዕቆብ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ያዕቆብ 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ያዕቆብ 5:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች