የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ያዕቆብ 4:1-12

ያዕቆብ 4:1-12 NASV

በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጉት ከምኞቶቻችሁ አይደለምን? ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም። ትገድላላችሁ፤ በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም። ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ፤ አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም። ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፣ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና። አመንዝሮች ሆይ፤ ከዓለም ጋራ ወዳጅነት ከእግዚአብሔር ጋራ ጠላትነት መሆኑን አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል። ወይስ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን? ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ያለው ስለዚህ ነው። እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁ፤ ዕዘኑ፤ አልቅሱም። ሣቃችሁ ወደ ሐዘን፣ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል። ወንድሞች ሆይ፤ እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን አድራጊ አይደለህም። ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?