ያዕቆብ 1:12-27

ያዕቆብ 1:12-27 NASV

በፈተና የሚጸና ሰው ብፁዕ ነው፤ ምክንያቱም ፈተናን ሲቋቋም እግዚአብሔር ለሚወድዱት የሰጠውን ተስፋ፣ የሕይወትን አክሊል ያገኛል። ማንም ሲፈተን፣ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ አትታለሉ። በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ፣ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ፤ በርሱ ዘንድ መለዋወጥ፣ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም። የፍጥረቱ በኵራት እንድንሆን በገዛ ፈቃዱ በእውነት ቃል ወለደን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህን አስተውሉ፤ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ፣ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣምና። ስለዚህ ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ። ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው ብሩክ ይሆናል። አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆችና ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች በችግራቸው መርዳትና ከዓለም ርኩሰት ራስን መጠበቅ ነው።