የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 63

63
እግዚአብሔር የሚቤዥበትና የሚበቀልበት ቀን
1ይህ ከኤዶም፣
ቀይ የተነከረ መጐናጸፊያ ለብሶ ከባሶራ የሚመጣ ማን ነው?
ይህ ክብርን የተጐናጸፈ፣
በኀይሉ ታላቅነት እየተራመደ የሚመጣውስ ማን ነው?
“በጽድቅ የምናገር፣
ለማዳንም ኀይል ያለኝ እኔው ነኝ።”
2መጐናጸፊያህ፣ ለምን በወይን መጭመቂያ፣
ወይን እንደሚረግጡ ሰዎች ልብስ ቀላ?
3“እኔ በመጭመቂያው ወይኑን ብቻዬን ረገጥሁ፤
ከመንግሥታት ማንም ከእኔ ጋር አልነበረም፤
በቍጣዬ ረገጥኋቸው፤
በመዓቴም ጨፈለቅኋቸው፤
ደማቸው በመጐናጸፊያዬ ላይ ተረጭቷል፤
ልብሴንም በክዬዋለሁ።
4የበቀል ቀን በልቤ አለ፤
የምቤዥበትም ዓመት ደርሷል።
5ተመለከትሁ፤ የሚረዳ ግን አልነበረም፤
የሚያግዝ ባለመኖሩም ተገረምሁ፤
ስለዚህ የገዛ ክንዴ ድነትን አመጣልኝ፤
የገዛ ቍጣዬም አጸናኝ፤
6መንግሥታትን በቍጣዬ ረጋገጥሁ፤
በመዓቴም አሰከርኋቸው፤
ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስሁ።”
ውዳሴና ጸሎት
7 የእግዚአብሔርን ቸርነት፣
እግዚአብሔር ስላደረገልን ሁሉ፣
ስለሚመሰገንበት ሥራው፣
እንደ ፍቅሩና እንደ ቸርነቱ መጠን፣
ለእስራኤል ቤት ያደረገውን፣
አዎን፣ ስላደረገው መልካም ነገር እናገራለሁ።
8እርሱም፣ “ርግጥ ነው፤ እነርሱ ሕዝቤ ናቸው፤
የማይዋሹኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው” አለ።
ስለዚህም አዳኝ ሆነላቸው።
9በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ፤
የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤
በፍቅሩና በምሕረቱ ዋጃቸው፤
በቀደመው ዘመን ሁሉ አነሣቸው፤
ተሸከማቸውም።
10እነርሱ ግን ዐመፁ፤
ቅዱስ መንፈሱንም አሳዘኑ፤
ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፤
እርሱ ራሱ ተዋጋቸው።
11ከዚያም ሕዝቡ የጥንቱን ዘመን፣
የሙሴንና የሕዝቡን ጊዜ እንዲህ በማለት አስታወሱ፤
የበጎቹን እረኛ፣
ከባሕሩ ያወጣቸው እርሱ የት አለ?
ቅዱስ መንፈሱንም፣
በመካከላቸው ያኖረ እርሱ የት አለ?
12የከበረው ኀያል ክንድ፣
በሙሴ ቀኝ እጅ ላይ እንዲያርፍ አደረገ፤
ለራሱ የዘላለም ዝና እንዲሆንለት፣
ውሆችን በፊታቸው ከፈለ።
13ፈረስ በምድረ በዳ እንደሚያልፍ ሁሉ፣
እነርሱንም በጥልቁ ውስጥ አሳልፎ መራቸው፤
ስለዚህም አልተሰናከሉም፤
14ወደ ሸለቆ እንደሚወርድ የከብት መንጋ፣
በእግዚአብሔር መንፈስ ዕረፍት ተሰጣቸው።
ሕዝብህን በዚህ ሁኔታ የመራሃቸው፣
ስምህን የከበረ ለማድረግ ነው።
15ከተቀደሰው፣ ከተከበረውና ከፍ ካለው ዙፋንህ፣
ከሰማይ ወደ ታች ተመልከት፤
ኀይልህና ቅናትህ የት አለ?
ገርነትህና ርኅራኄህ ከእኛ ርቀዋል።
16አብርሃም ባያውቀን፣
እስራኤልም ባያስታውሰን እንኳ፣
አንተ እኮ አባታችን ነህ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤
ከጥንትም ቢሆን ስምህ “ቤዛችን” ነው።
17 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከመንገድህ እንድንወጣ፣
ልባችንን በማደንደን ለምን እንዳንፈራህ አደረግኸን?
ስለ ባሮችህ ስትል፣
ስለ ርስትህ ነገዶች ስትል እባክህ ተመለስ።
18ለጥቂት ጊዜ ሕዝብህ የተቀደሰውን ስፍራ ወርሶ ነበር፤
አሁን ግን ጠላቶቻችን መቅደስህን ረገጡት።
19እኛ እኮ ጥንትም የአንተው ነን፤
እነርሱን ግን አንተ አላገዝሃቸውም፤
በስምህም አልተጠሩም።#63፥19 ወይም፣ አንተ እንዳልገዛሃቸው እንመስላለን፣ ልክ በአንተ ስም እንዳልተጠሩት

Currently Selected:

ኢሳይያስ 63: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ