ኢሳይያስ 59
59
ኀጢአት፣ ንስሓና መቤዠት
1እነሆ፤ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤
ጆሮውም መስማት አልተሳናትም።
2ነገር ግን በደላችሁ
ከአምላካችሁ ለይቷችኋል፤
ኀጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፤
በዚህም ምክንያት አይሰማም።
3እጆቻችሁ በደም፣
ጣቶቻችሁ በበደል ተነክረዋል፤
ከንፈሮቻችሁ ሐሰትን ተናገሩ፤
ምላሶቻችሁ ክፉ ነገርን አሰሙ።
4ፍትሕን የሚጠራ ማንም የለም፤
ጕዳዩን በቅንነት የሚያቀርብ የለም፤
በከንቱ ነገር ታመኑ፤ ሐሰትን ተናገሩ፤
ሁከትን ፀነሱ፤ ክፋትንም ወለዱ።
5የእባብ ዕንቍላል ታቀፉ፤
የሸረሪት ድር ዐደሩ፤
ዕንቍላሎቻቸውን የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤
አንዱ በተሰበረ ጊዜም እፉኝት ይወጣል።
6ድሮቻቸው ልብስ አይሆኑም፤
በሚሠሩትም ሰውነታቸውን መሸፈን አይችሉም፤
ሥራቸው ክፉ ነው፤
እጃቸውም በዐመፅ ሥራ የተሞላ ነው።
7እግሮቻቸው ወደ ኀጢአት ይሮጣሉ፤
ንጹሕ ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤
የሚያስቡት ክፉ ሐሳብ ነው፤
ማጥፋትና ማፈራረስም የመንገዳቸው ምልክት ነው።
8የሰላምን መንገድ አያውቁም፤
በጐዳናቸውም ፍትሕ የለም፤
መንገዳቸውን ጠማማ አድርገውታል፤
በዚያም የሚሄድ ሰላም አያገኝም።
9ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቋል፤
ጽድቅም ወደ እኛ አይመጣም፤
ብርሃንን ፈለግን፤ ነገር ግን ሁሉ ጨለማ ነው፤
የብርሃንን ጸዳል ፈለግን፤ የምንሄደው ግን በድንግዝግዝታ ነው።
10በቅጥሩ ላይ እንደ ዕውር ተደናበርን፤
አካሄዳችንም ዐይን እንደሌላቸው በዳበሳ ሆነ፤
ጀንበር በምትጠልቅበት ጊዜ እንደሚሆነው በእኩለ ቀን ተደናበርን፤
በብርቱዎች መካከልም እንደ ሙታን ሆንን።
11ሁላችን እንደ ድቦች እናላዝናለን፤
እንደ ርግቦችም በመቃተት እንጮኻለን፤
ፍትሕን ፈለግን፤ ግን አላገኘንም፤
ትድግናን ፈለግን፤ ነገር ግን ከእኛ ርቋል።
12በደላችን በፊትህ በዝቷል፤
ኀጢአታችን መስክሮብናል፤
በደላችን ከእኛ አልተለየም፤
ዐመፀኝነታችንንም እናውቃለን።
13በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀናል፤ ሐሰት ተናግረናል፤
አምላካችንን ከመከተል ዘወር ብለናል፤
ዐመፃንና ግፍን አውርተናል፤
ልባችን የፀነሰውን ውሸት ተናግረናል።
14ስለዚህ ፍትሕ ከእኛ ርቋል፤
ጽድቅም በሩቁ ቆሟል፤
እውነት በመንገድ ላይ ተሰናክሏል፤
ቅንነትም መግባት አልቻለም።
15እውነት የትም ቦታ አይገኝም፤
ከክፋት የሚርቅ ለጥቃት የተጋለጠ ነው።
እግዚአብሔር ተመለከተ፤
ፍትሕ በመታጣቱም ዐዘነ።
16ማንም እንደሌለ አየ፤
ወደ እርሱ የሚማልድ ባለመኖሩ ተገረመ፤
ስለዚህ የገዛ ክንዱ ድነት አመጣለት፤
የራሱም ጽድቅ ደግፎ ያዘው።
17ጽድቅን እንደ ጥሩር አጠለቀ፤
የድነትን ቍር በራሱ ላይ ደፋ፤
የበቀልንም ልብስ ለበሰ፤
መጐናጸፊያ እንደሚደረብም ቅናትን ደረበ።
18እንደ ሥራቸው መጠን፣
ቍጣን ለባላጋራዎቹ፣
ፍዳን ለጠላቶቹ፣
እንደዚሁ ይከፍላቸዋል፤
ለደሴቶችም የእጃቸውን ይሰጣቸዋል።
19በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም ይፈራሉ፤
በፀሓይ መውጫ ያሉት ለክብሩ ይገዛሉ፤
የእግዚአብሔር እስትንፋስ እንደ ተቋተ፣
እንደ ተከማቸም ጐርፍ ይመጣልና።#59፥19 ወይም፣ ጠላት እንደ ጐርፍ በሚመጣበት ጊዜ/የእግዚአብሔር መንፈስ በውጊያ ያዋርደዋል
20“አዳኝ ወደ ጽዮን፣
ኀጢአታቸውንም ወደ ተናዘዙት ወደ ያዕቆብ ቤት ይመጣል”
ይላል እግዚአብሔር።
21“በእኔ በኩል፣ ከእነርሱ ጋር ያለኝ ቃል ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “በአንተም ላይ ያለው መንፈሴ፣ በአፍህ ያስቀመጥሁት ቃሌ ከአፍህ፣ ከልጆችህ አፍ፣ ከዘር ዘሮቻቸውም አፍ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም አይለይም” ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ኢሳይያስ 59: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.