የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 58

58
እውነተኛ ጾም
1“በኀይል ጩኽ፤ ምንም አታስቀር፤
ድምፅህን እንደ መለከት አሰማ፤
ለሕዝቤ ዐመፃቸውን፣
ለያዕቆብም ቤት ኀጢአታቸውን ተናገር።
2ዕለት በዕለት ይፈልጉኛል፤
መንገዴን ለማወቅ የሚጓጉ ይመስላሉ፤
ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ፣
የአምላኩንም ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ሁሉ፣
ተገቢ የሆነ ፍትሕ ይለምኑኛል፤
እግዚአብሔር ወደ እነርሱ እንዲቀርብ የሚወድዱም ይመስላሉ።
3‘አንተ ካልተቀበልኸው፣
ስለ ምን ብለን ጾምን?
አንተ ከጕዳይ ካልቈጠርኸው፣
ስለ ምን ራሳችንን አዋረድን?’ ይላሉ።
“ሆኖም በጾማችሁ ቀን የልባችሁን ታደርጋላችሁ፤
ሠራተኞቻችሁንም ትበዘብዛላችሁ።
4ጾማችሁ በጥልና በክርክር፣
በግፍ ጡጫና በመደባደብ ይፈጸማል፤
ከእንግዲህ ዛሬ እንደምትጾሙት ጾማችሁ፣
ድምፃችሁ ወደ ላይ እንደሚሰማ ተስፋ አታድርጉ።
5እኔ የመረጥሁት ጾም እንዲህ ዐይነቱን ነውን?
ሰውስ ራሱን የሚያዋርደው በእንዲህ ያለው ቀን ብቻ ነውን?
እንደ ደንገል ራስን ዝቅ ማድረግ ነውን?
ወይስ ማቅ ለብሶ በዐመድ ላይ መንከባለል ነውን?
ታዲያ ጾም ብለህ የምትጠራው ይህን ነውን?
እግዚአብሔርስ የሚቀበለው እንዲህ ያለውን ቀን ነውን?
6“እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣
የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣
የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣
የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣
ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን?
7ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣
ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣
የተራቈተውን ስታይ እንድታለብሰው፣
የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሣው አይደለምን?
8ይህ ከሆነ ብርሃንህ እንደ ንጋት ጮራ ይፈነጥቃል፤
ፈውስህ ፈጥኖ ይደርሳል፤
ጽድቅህ#58፥8 ወይም የአንተ ጻድቁ ቀድሞህ ይሄዳል፤
የእግዚአብሔር ክብር ደጀን ይሆንልሃል።
9የዚያን ጊዜ ትጣራለህ፤ እግዚአብሔርም ይመልስልሃል፤
ለርዳታ ትጮኻለህ፤ እርሱም፣ ‘አለሁልህ’ ይልሃል።
“የጭቈና ቀንበር፣
የክፋትን ንግግርና ጣት መቀሰርን ከአንተ ብታርቅ፣
10ለተራበው ብትራራለት፣
የተገፉት እንዲጠግቡ ብታደርግ፣
ብርሃንህ በጨለማ ያበራል፤
ሌሊትህም እንደ ቀትር ፀሓይ ይሆናል።
11 እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤
ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤
ዐጥንትህን ያበረታል፤
በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣
እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።
12ወገኖችህ የቀድሞ ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤
የጥንቱንም መሠረት ያቆማሉ፤
አንተም፣ የተናዱ ቅጥሮችን አዳሽ፣
ባለ አውራ መንገድ ከተሞችን ጠጋኝ ትባላለህ።
13“እግሮችህ ሰንበትን እንዳይሽሩ ብታሳርፍ፣
በተቀደሰው ቀኔ የልብህን ባታደርግ፣
ሰንበትን ደስታ፣
የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቀን የተከበረ ብለህ ብትጠራው፣
በገዛ መንገድህ ከመሄድ፣
እንደ ፈቃድህ ከማድረግና ከከንቱ ንግግር ብትቈጠብ፣
14በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤
በምድር ከፍታዎች ላይ እንድትጋልብ፣
የአባትህን የያዕቆብን ርስት ጠግበህ እንድትበላ አደርግሃለሁ”
የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 58: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ