የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 44:1-8

ኢሳይያስ 44:1-8 NASV

“ነገር ግን አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ፣ የመረጥሁህ እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ የፈጠረህ፣ በማሕፀን የሠራህ፣ የሚረዳህ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ባሪያዬ ያዕቆብ፣ የመረጥሁህ ይሹሩን ሆይ፣ አትፍራ። በተጠማ ምድር ላይ ውሃ፤ በደረቅ መሬት ላይ ወንዞችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ፣ በረከቴንም በልጅ ልጅህ ላይ አወርዳለሁ። እነርሱም በለመለመ መስክ ላይ እንደ ሣር፣ በወንዝ ዳር እንደ አኻያ ዛፍ ይበቅላሉ። አንዱ፣ ‘እኔ የእግዚአብሔር ነኝ’ ይላል፤ ሌላው ራሱን በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ሌላው ደግሞ በእጁ ላይ ‘የእግዚአብሔር ነኝ’ ብሎ ይጽፋል፤ ራሱን በእስራኤል ስም ይጠራል። እግዚአብሔር “የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም። እስኪ እንደ እኔ ማን አለ? ይናገር፤ ሕዝቤን ከጥንት ስመሠርት ምን እንደ ነበረ፣ ገና ወደ ፊት ምን እንደሚሆን፣ ይናገር፤ በፊቴ ያስረዳ፤ ስለሚመጣውም ነገር አስቀድሞ ይናገር። አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ ይህን አልነገርኋችሁምን? ቀድሞስ አላሳወቅኋችሁምን? ለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ! ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።”