ኢሳይያስ 42:1-9

ኢሳይያስ 42:1-9 NASV

“እነሆ፤ ደግፌ የያዝሁት፣ በርሱም ደስ የሚለኝ የመረጥሁት አገልጋዬ፤ መንፈሴን በርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል። አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም። የተቀጠቀጠ ሸንበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል። ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣ አይደክምም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤ ደሴቶች በሕጉ ይታመናሉ።” ሰማያትን የፈጠረ፣ የዘረጋቸውም፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ፣ ለሕዝቧ እስትንፋስን፣ ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ። የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ። “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው! ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም። እነሆ፤ የቀድሞው ነገር ተፈጽሟል፤ እኔም አዲስ ነገር እናገራለሁ፤ ከመብቀሉም በፊት፣ ለእናንተ አስታውቃለሁ።”