ኢሳይያስ 39
39
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
1በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ፣ የባልዳን ልጅ፣ መሮዳክ ባልዳን የሕዝቅያስን መታመምና መፈወስ ሰምቶ ስለ ነበር፣ ደብዳቤና ስጦታ ላከለት። 2ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበለ፤ ለእነርሱም በግምጃ ቤቱ ውስጥ ያለውን ብሩን፣ ወርቁን፣ ቅመማ ቅመሙን፣ ምርጡን ዘይት እንዲሁም የጦር መሣሪያውን በሙሉ፣ ያለውንም ንብረት አንዳች ሳያስቀር አሳያቸው። በቤተ መንግሥቱም ሆነ በግዛቱ ሁሉ ሕዝቅያስ ያላሳያቸው ነገር አልነበረም።
3ከዚያም ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ መጥቶ፣ “እነዚያ ሰዎች ምን አሉህ? ወደ አንተ ዘንድ የመጡትስ ከየት ነው?” አለው።
ሕዝቅያስም፣ “ወደ እኔ የመጡት ከሩቅ አገር፣ ከባቢሎን ነው” አለው።
4ነቢዩም፣ “በቤተ መንግሥትህ ያዩት ምንድን ነው?” አለው።
ሕዝቅያስም፣ “በቤተ መንግሥቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ ከንብረቴ ያላሳየኋቸው ምንም ነገር የለም” አለ።
5ኢሳይያስም ሕዝቅያስን እንዲህ አለው፤ “የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ 6እነሆ፤ በቤተ መንግሥትህ ያለው ሁሉ፣ አባቶችህ እስከዚህች ቀን ድረስ ያከማቹትም ሁሉ ወደ ባቢሎን ተማርኮ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፤ አንዳች የሚተርፍ ነገር የለም፤ ይላል እግዚአብሔር። 7ከአብራክህ ከሚከፈሉት፣ ከዘርህ፣ ከአንተ ከሚወለዱት ልጆች ተወስደው፣ በባቢሎን ንጉሥ ቤተ መንግሥት ጃንደረባዎች ይሆናሉ።”
8ሕዝቅያስም፣ “የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው” አለው፤ “በዘመኔ ሰላምና ጸጥታ ከኖረ ዘንድ” ብሎ ዐስቦ ነበርና።
Currently Selected:
ኢሳይያስ 39: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.