የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 37

37
የኢየሩሳሌም ዐርነት ታወጀ
1ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። 2ከዚያም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፣ ጸሓፊውን ሳምናስንና ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። 3እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ልጆች ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኗል። 4ምናልባት ሕያው አምላክን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።’ ”
5የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤ 6ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር። 7እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”
8የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ትቶ መሄዱን ሲሰማ ተመለሰ፤ ንጉሡም ልብናን ሲወጋ አገኘው።
9ደግሞም ሰናክሬም፣ የኢትዮጵያ#37፥9 የላይኛውን የአባይ ወንዝ አካባቢ ያመላክታል። ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋው መምጣቱን ሰማ፤ ይህንም እንደ ሰማ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤ 10“ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልልህ። 11እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 12የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን? 13የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄና ንጉሥ ወይም የዒዋ ንጉሥ የት አሉ?”
የሕዝቅያስ ጸሎት
14ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶም ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ 16“በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል። 17አቤቱ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብልና ስማ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈትና እይ። ሰናክሬም ሕያው አምላክን ለመሳደብ የላከውን ቃል ሁሉ ስማ።
18እግዚአብሔር ሆይ፤ የአሦር ነገሥታት እውነትም እነዚህን አሕዛብንና ምድራቸውን አጥፍተዋል። 19አማልክታቸውን ወደ እሳት ጥለዋል፤ በሰው እጅ የተቀረጹ የድንጋይና የዕንጨት ምስሎች እንጂ አማልክት አልነበሩምና። 20አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆንህን ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”
የሰናክሬም ውድቀት
21ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ስለ አሦር ንጉሥ፣ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ጸልየሃልና፣ 22እግዚአብሔር በርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤
“ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣
ንቃሃለች፣ ታቃልልሃለችም፤
የኢየሩሳሌም ልጅ፣
አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች።
23የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው?
ድምፅህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው፣
ዐይንህን በትዕቢት ያነሣኸው በማን ላይ ነው?
በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እኮ!
24በመልእክተኞችህ በኩል፣
በጌታ ላይ ብዙ የስድብ ቃል ተናገርህ፤
እንዲህም አልህ፤
‘በሠረገሎቼ ብዛት፣
የተራሮችንም ከፍታ፣
የሊባኖስንም ጫፍ ወጥቻለሁ፤
ረዣዥም ዝግባዎችን፣
የተመረጡ ጥዶችን ቈርጫለሁ፤
እጅግ ወደራቁት ከፍታዎች፣
እጅግ ውብ ወደሆኑትም ደኖች ደርሻለሁ፤
25በባዕድ ምድር#37፥25 የሙት ባሕር ቅጆች (እንዲሁም 2ነገ 19፥24 ይመ፤) ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ በባዕድ ምድር የሚለውን ሐረግ አይጨምርም። የውሃ ጕድጓዶችን ቈፈርሁ፤
በዚያም ውሃ ጠጣሁ።
የግብጽን ምንጮች ሁሉ፣
በእግሬ ረግጬ አደረቅሁ።’
26“ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣
አልሰማህምን?
ጥንትም እንዳቀድሁት
አሁን ግን እንዲፈጸም አደረግሁት፤
ይህም የተመሸጉትን ከተሞች አንተ የድንጋይ
ክምር ማድረግህ ነው።
27የሕዝቦቻቸው ኀይል ተሟጥጧል፤
ደንግጠዋል፤ ተዋርደዋልም፤
በሜዳ እንዳሉ ዕፀዋት፣
እንደ ለጋ ቡቃያ፣
በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፣
በእንጭጩ ዋግ እንደ መታው ሆነዋል።
28“ ‘እኔ ግን የት እንዳለህ፣
መቼ እንደምትመጣና መቼ እንደምትሄድ፣
በእኔም ላይ እንዴት በቍጣ እንደምትነሣሣ ዐውቃለሁ።
29በእኔ ላይ በቍጣ ስለ ተነሣሣህ፣
እብሪትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣
ስናጋዬን በአፍንጫህ አደርጋለሁ፣
ልጓሜን በአፍህ አስገባለሁ፤
በመጣህበትም መንገድ እንድትመለስ
አደርግሃለሁ።’
30“ሕዝቅያስ ሆይ፤ ይህ ምልክት ይሆንልሃል፤
“በዚህ ዓመት የገቦውን፣
በሚቀጥለው ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤
በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤
ወይን ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።
31እንደ ገናም የይሁዳ ቤት ቅሬታ፣
ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፤ ከላይም ፍሬ ያፈራል፤
32ቅሬታ የሆኑት ከኢየሩሳሌም፣
የተረፉትም ከጽዮን ተራራ ይመጣሉና፤
የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅናት
ይህን ያደርጋል።
33“ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤
“ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባም፤
ፍላጻም አይወረውርባትም፤
ጋሻ አንግቦ አይቀርብም፤
በዐፈርም ቍልል አይከብባትም።
34በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤
ወደዚህች ከተማም አይገባም”
ይላል እግዚአብሔር
35“ስለ ራሴና፣ ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል፣
ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ፤ አድናታለሁም።”
36ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያን ሰፈር አንድ መቶ ሰማንያ ዐምስት ሺሕ ሰው ገደለ፤ ሰዎቹ ማለዳ ሲነሡ፤ ቦታው ሬሳ በሬሳ ነበር። 37ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ነነዌም ተመልሶ በዚያ ተቀመጠ።
38ናሳራክ በተባለው አምላኩ ቤተ ጣዖት ገብቶ በመስገድ ላይ ሳለ፣ አድራሜሌክና ሳራሳር የተባሉ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት፤ ከዚያም አምልጠው ወደ አራራት ሸሹ። ልጁ አስራዶንም በምትኩ ነገሠ።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 37: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ