የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 19

19
ስለ ግብፅ የተነገረ ትንቢት
1ስለ ግብፅ የተነገረ ንግር፤
እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ
ወደ ግብፅ ይመጣል፤
የግብፅ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤
የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
2“ግብፃዊውን በግብፃዊው ላይ አስነሣለሁ፤
ወንድም ወንድሙን፣
ባልንጀራ ባልንጀራውን፣
ከተማም ከተማን፣
መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።
3የግብፃውያን ልብ ይሰለባል፤
ዕቅዳቸውንም መና አስቀራለሁ፤
እነርሱም ጣዖታትንና የሙታንን መናፍስት፣
መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ምክር ይጠይቃሉ።
4ግብፃውያንን አሳልፌ
ለጨካኝ ጌታ ክንድ እሰጣቸዋለሁ፤
አስፈሪ ንጉሥም ይገዛቸዋል”
ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
5የአባይ ወንዝ ይቀንሳል፤
ውሃውም እየጐደለ ይሄዳል።
6መስኖዎቹ ይከረፋሉ፤
የግብፅ ጅረቶች ይጐድላሉ፤ ይጠፋሉም።
ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል፤
7እንዲሁም በአባይ ዳር፣
በወንዙ መፋሰሻ ላይ ያሉት ተክሎች ይጠወልጋሉ።
በአባይ ዳር የተዘራው ዕርሻ ሁሉ፣
በነፋስ ይወሰዳል፤ ምንም አይቀርም።
8ዓሣ አጥማጆች ያዝናሉ፤
በአባይ ወንዝ ላይ መንጠቋቸውን የሚወረውሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤
በውሃ ላይ መረባቸውን የሚጥሉ ሁሉ፣
ጕልበታቸው ይዝላል።
9የተነደፈ የተልባ እግር የሚፈትሉ፣
የተባዘተ ጥጥ የሚሠሩ ሸማኔዎችም ተስፋ ይቈርጣሉ።
10ልብስ ሠሪዎች ያዝናሉ፤
ደመወዝተኞችም ልባቸው ይሰበራል።
11የጣኔዎስ አለቆች በጣም ሞኞች ናቸው፤
የፈርዖን ጠቢባን ምክራቸው የማይረባ ነው፤
ፈርዖንን፣ “እኔ ከጥበበኞች አንዱ ነኝ፤
የጥንት ነገሥታትም ደቀ መዝሙር ነኝ”
እንዴት ትሉታላችሁ?
12የእናንተ ጠቢባን አሁን የት አሉ?
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
በግብፅ ላይ ያሰበውን ነገር፣
እስቲ ያሳዩአችሁ፤ ያሳውቋችሁም።
13የጣኔዎስ አለቆች ተሞኝተዋል፤
የሜምፊስ ሹማምት ተታልለዋል፤
የሕዝቧ ዋና ዋናዎች፣
ግብፅን አስተዋታል።
14 እግዚአብሔር የድንዛዜን መንፈስ አፍስሶባቸዋል፤
ሰካራም በትፋቱ ዙሪያ እንደሚንገዳገድ፣
ግብፅንም በምታደርገው ነገር ሁሉ
እንድትንገዳገድ አደረጓት።
15ራስም ይሁን ጅራት፣ የዘንባባ ዝንጣፊም ይሁን ደንገል፣
ለግብፅ የሚያደርጉላት አንዳች ነገር የለም።
16በዚያን ቀን ግብፃውያን እንደ ሴት ይሆናሉ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ካነሣው ክንዱ የተነሣ በፍርሀት ይንቀጠቀጣሉ። 17የይሁዳ ምድር በግብፅ ላይ ሽብር ትነዛለች፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ካቀደው የተነሣ፣ ስለ ይሁዳ ወሬ የሰማ ሁሉ ይሸበራል።
18በዚያ ቀን አምስት የግብፅ ከተሞች በከነዓን ቋንቋ ይናገራሉ፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርም ወገን ለመሆን ቃል ኪዳን ይገባሉ፤ ከእነዚህም ከተሞች አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።
19በዚያ ቀን በግብፅ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ላይ ለእግዚአብሔር ዐምድ ይቆማል። 20ይህም በግብፅ ምድር ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቋቸውም የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፣ አዳኝና ታዳጊ ይልክላቸዋል፤ እርሱም ያድናቸዋል። 21እግዚአብሔር ራሱን ለግብፃውያን ይገልጣል፤ እነርሱም በዚያ ቀን እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ በመሥዋዕትና በእህል ቍርባንም ያመልኩታል። ለእግዚአብሔር ስለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽሙታል። 22እግዚአብሔር ግብፅን በመቅሠፍት ይመታታል፤ መትቶም፤ ይፈውሳቸዋል። እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።
23በዚያ ቀን ከግብፅ ወደ አሦር አውራ መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራውያን ወደ ግብፅ፣ ግብፃውያንም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብፃውያንና አሦራውያን በአንድነት ያመልካሉ። 24በዚያ ቀን እስራኤል፣ ከግብፅና ከአሦር ጋር የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች። 25የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርም፣ “ሕዝቤ ግብፅ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 19: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ