የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሆሴዕ 13

13
የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ
1ኤፍሬም ሲናገር ሰዎች ተንቀጠቀጡ፤
በእስራኤልም የተከበረ ነበር፤
ነገር ግን በኣልን ስላመለከ በደለ፤ ሞተም።
2አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤
ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣
በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤
ሁሉም የባለ እጅ ሥራ ናቸው።
ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሏል፤
“ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤
የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ”#13፥2 ወይም መሥዋዕት የሚያቀርቡ ሰዎች… ይስማሉ
3ስለዚህ እንደ ማለዳ ጉም፣
ፈጥኖ እንደሚጠፋ የጧት ጤዛ፣
ከዐውድማ እንደሚጠረግ እብቅ፣
በመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ።
4“እኔ ግን ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ፣#13፥4 ወይም በግብፅ ከነበራችሁበት ጊዜ አንሥቶ
አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤
ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፤
ከእኔም በቀር ሌላ አዳኝ የለም።
5በምድረ በዳ፣
በሐሩር ምድርም ተንከባከብሁህ።
6ካበላኋቸው በኋላ ጠገቡ፤
በጠገቡ ጊዜ ታበዩ፤
ከዚያም ረሱኝ።
7ስለዚህ እንደ አንበሳ እመጣባቸዋለሁ፤
እንደ ነብርም በመንገድ አደባባቸዋለሁ።
8ግልገሎቿን እንደ ተነጠቀች ድብ፣
እመታቸዋለሁ፤ እዘነጣጥላቸዋለሁ።
እንደ አንበሳም ሰልቅጬ እውጣቸዋለሁ፤
የዱር አራዊትም ይገነጣጥላቸዋል።
9“እስራኤል ሆይ፤ በእኔ ላይ ስለ ተነሣህ፣
ረዳትህንም ስለ ተቃወምህ ትጠፋለህ።
10‘ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ፤’
ብለህ እንደ ጠየቅኸው፣
ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ የት አለ?
በከተሞችህ ሁሉ የነበሩ ገዦችህስ የት አሉ?
11በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፤
በመዓቴም ሻርሁት።
12የኤፍሬም በደል ተከማችቷል፤
ኀጢአቱም በመዝገብ ተይዟል።
13በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤
እርሱ ግን ጥበብ የሌለው ልጅ ነው፤
የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ፣
ከእናቱ ማሕፀን መውጣት የማይፈልግ ሕፃን ነው።
14“ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤
ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤
ሞት ሆይ፤ መቅሠፍትህ የት አለ?
መቃብር ሆይ፤#13፥14 በዕብራይስጥ ሲኦል ማለት ነው ማጥፋትህ የት አለ?
“ከእንግዲህ ወዲህ አልራራለትም፤
15በወንድሞቹ መካከል ቢበለጽግም እንኳ፣
የምሥራቅ ነፋስ ከምድረ በዳ እየነፈሰ፣
ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል፤
ምንጩ ይነጥፋል፤
የውሃ ጕድጓዱም ይደርቃል።
የከበረው ሀብቱ ሁሉ፣
ከግምጃ ቤቱ ይበዘበዛል።
16የሰማርያ ሰዎች በደላቸውን ይሸከማሉ፤
በአምላካቸው ላይ ዐምፀዋልና፤
በሰይፍ ይወድቃሉ፤
ሕፃኖቻቸውም በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤
የእርጉዝ ሴቶቻቸውም ሆድ ይቀደዳል።”

Currently Selected:

ሆሴዕ 13: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ