ዕብራውያን 8:6-13

ዕብራውያን 8:6-13 NASV

ነገር ግን ኢየሱስ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን ከቀድሞው እንደሚበልጥ ሁሉ፣ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፤ ይህም የተመሠረተው በተሻለ የተስፋ ቃል ላይ ነው። የመጀመሪያው ኪዳን ምንም ጕድለት ባይገኝበት ኖሮ፣ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ጕድለት በማግኘቱ እንዲህ ይላቸዋል፤ “ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ፣ አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል፤ ይላል ጌታ። ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣ እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ ምክንያቱም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑም፤ እኔም ከእነርሱ ዘወር አልሁ፤ ይላል ጌታ። ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ከእንግዲህ ማንም ሰው ጎረቤቱን ወይም ወንድሙን፣ ‘ጌታን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ ምክንያቱም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ፣ ሁሉም ያውቁኛል። በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስብም።” ይህን ኪዳን፣ “አዲስ” በማለቱ የፊተኛውን ኪዳን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ያረጀ ያፈጀው የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።